የአሸባሪውን ቡድን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን በፈቃዳችን እንዘምታለን

ሕዳር 5/2014 (ኢዜአ) የአሸባሪውን ቡድን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን በፈቃዳቸው እንደሚዘምቱ ከደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ገለጹ፡፡

የደቡብ ክልል ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአገር ህልውና ዘመቻው እንዲሳተፉ ዛሬ ሽኝት አድርጎላቸዋል፡፡

በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ ሰራዊት አባላት የአሸባሪውን ቡድን ግብዓተ መሬት በማፋጠን የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ እንደሚዘምቱ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸውን የገለጹት አባላቱ፤አሁንም ኢትዮጵያ ከገጠማት ፈተና ተላቃ ወደ ዕድገት እንድታመራ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል፡፡

አሸባሪውን ቡድን ከአፋርና ከአማራ ክልል በማስወጣት ዳግም ለዜጎች ስጋት በማይሆንበት ደረጃ እስኪደርስ እንደመስሰዋልን ብለዋል፡፡

መቼም ቢሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ትናንትም በማንም ተደፍራ አታውቅም ያሉት ዘማቾቹ ዛሬም በእኛ ዘመን አገራችን እንዳትደፈር ሁሉንም መስዋዕትነት እንከፍላለን ሲሉ ተናግረዋል።

እኛ ከአባቶቻችን የተቀበልናትን አገር በማንም ሳናስደፍር ጠብቀን ለመጪው ትውልድ እናስተላልፋለን ብለዋል፡፡

ወጣቱ አገሩን ከእኛ ተረክቦ ለመጠበቅ መዘጋጀት ይኖርበታል ሲሉም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ህዝቡም አንድነቱን በመጠበቅ አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች መከላከል እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

የሽኝት መርሃ ግብሩ በዛሬው ዕለት በጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም