የሽብር ቡድኖችን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ሁሉ አቀፍ እገዛችን አይለይም - ኢዜአ አማርኛ
የሽብር ቡድኖችን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ሁሉ አቀፍ እገዛችን አይለይም

ደብረ ብርሃን ህዳር 5/ 2014 (ኢዜአ) የህውሓትና የሸኔ ሀገር የማፍረስ እኩይ ሴራን ለማክሸፍ በሚደረገው ርብርብ በገንዘብም ሆነ በጉልበታቸው የሚችሉትን ሁሉ ለመደገፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ የደብረ ብርሃን ከተማ ነጋዴዎች ገለፁ።
የከተማው አስተዳደሩ ዛሬ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት አካሄዷል።
የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ዮናስ ከበደ ለኢዜአ እንደገለፁት ከሶሰት ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ የተመዘገበው ለውጥ ሀገሪቱን ወደ ቀደመው ገናና ታሪኳ ለመመለስ የሚያስችል አካታች መንገድ ተከፍቷል።
ነገር ግን በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ ያልተዋጠላቸው የህወሓትና ሸኔ ሀገር የማፍረስና ሕዝብን የማሰቃየት እኩይ ሴራቸውን ሸርበው በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ታሪክ የማይረሳው በደል ፈጽመዋል፤ እየፈፀሙም ይገኛሉ።

የአሸባሪቹን እኩይ ሴራ በማክሸፍ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማዋ ለማውጣት ከመንግሥት ጎን በመሆን ጠላትን ለመመከት እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት ለህልውና ዘመቻው የአቅማቸውን በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን ማበርከታቸውን አስታውሰው፤ አሁንም ገንዘብ ከማዋጣት ጀምሮ አስከ ህይወት መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ሌላው ተሳታፊ አቶ ይልማ ሸዋ ምንአለ በበኩላቸው ህውሓት ሀገር የማፍረስ ሴራው እኛ በህይወት እያለን አይሳካለትም፤ ብለዋል።
ሀገር የምትፈርሰው በህዝብ የተመረጠ መንግሥት በሌለ ጊዜ እንጂ ህዝብ ወዶ የመረጠው ጠንካራና ባለራዕይ መንግሥት የሚመራ ሀገር እንደማይፈርስ ገልፀዋል።
አሸባሪቹ ህውሓትና ሸኔ የሚያካሂዱትን የውክልና ጦርነት በአጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ በመንግሥት የሚጠየቁትን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሰርጎ ገቦችን በመከታተልና በመቆጣጠር የከተማዋን ሰላም ለማስከበር ከመስራት ጎን ለጎን በምግብ እህልና በሸቀጦች ላይ ነጋዴው ያልተገባ ዋጋ እንዳይጨምር የእርስ በርስ ቁጥጥር እያደረግን ነው ብለዋል።
''የህውሓትን ሀገር አፍራሽ ሴራ እስከነ ክፉ አስተሳሰቡ ለመቅበር የነጋዴው ድጋፍ ከፍተኛ ነው'' ያሉት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ ናቸው።
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያካሂደውን ጦርነትን ለመመከት ነጋዴው ህብረተሰብ እስካሁን ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የንግዱ ማህበረሰብ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ የሕልውና ዘመቻውን በተጠናከረ ሁኔታ ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።
በተለይም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ያልተገባ ዋጋ በመጨመርና ምርት በመደበቅ በሕዝብ ላይ የሚደረግ ግፍ ተጠያቂ ያደርጋል፤ ለዚህም ሁሉም ነጋዴ በኃላፊነት መንፈስ መስራትና ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ሲሉ ገልፀዋል።
በውይይቱ የከተማ አስተዳደሩ ነጋዴዎች፣ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።