አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ ግንባር በመዝመትና በደጀንነት ተሰልፈናል- የቅማንት ተወላጆች

57

ጎንደር ህዳር 5/2014 (ኢዜአ) የክተት ጥሪን ተቀብለው የህወሃት ወራሪ ሀይልን ለመደምሰስ በግንባር በመዝመትና በደጀንነት በመሰለፍ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በማእከላዊ ጎንደር ዞን በላይ አርማጭሆ ወረዳ የሚገኙ የቅማንት ተወላጆች አስታወቁ፡፡

ተወላጆቹ በህልውና ዘመቻው በጀግንነት ሲፋለሙ ጉዳት ደርሶባቸው በጎንደር ከተማ ህክምና ለሚከታተሉ የጸጥታ አካላት የእርድ እንስሳትን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ዛሬ አድርገዋል፡፡

ድጋፉን ካስተባበሩ የቅማንት ተወላጆች መካከል ወጣት ዳንኤል አረጋ ለኢዜአ እንደገለጸው ቅድሚያ ለሀገራችን ህልውና በመስጠት የክተት ጥሪውን ተቀብለን እየደገፍን ነው፡፡

ሽበርተኛው ህወሃት በአማራና ቅማንት ህዝብ መካከል ክፍፍል በመፍጠር ሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት የገነቡትን የአብሮነት እሴት በመናድ የራሱን ህለውና ለማስቀጠል ከፍተኛ ሴራና ደባ ሲፈጽም መቆየቱን ተናግረዋል።

የቅማንት ህዝብ የአሸባሪውን እኩይ ተግባር በመገንዘብ ከወንድሙ አማራ ጋር አንድነቱን በማጠናከር ዛሬ ላይ ወራሪውን በግንባር ከመፋለም ጀምሮ ሰፊ የደጀንነት አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ጥላነሽ ይማም በበኩላቸው የቅማንት ህዝብ የአሸባሪው ህወሃት ሴራ ሰለባ በመሆን ከአማራ ወገኑ ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ አላስፈላጊ መስዋእትነት ሲከፍል መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የህወሃት የጭካኔ ተግባር ተዘርዝሮ አያልቅም ያሉት ወይዘሮ ጥላነሽ " ሽብርተኛው ከአንድ ቤት በርካታ የቤተሰብ አባላትን ከመግደል ጀምሮ ሴቶችን በመድፈር፣ የሃይማኖት አባቶችን በመግደልና የእምነት ቦታዎችን በማራከስ የዘመኑ ፋሺስትነቱን በተግባር ያሳየ ነው" ብለዋል፡፡

"የቅማንት ህዝብ ከቶም ቢሆን የህወሃትን አላማ አያራምድም፤ ዛሬም ወረራውን ለመቀልበስና ግብአተ መሬቱን ለማጠናቀቅ በክተት ዘመቻው በግንባር ተሰልፎ መስዋእት በመሆን ህዝባዊ አንድነቱን በተግባር እያረጋጋጠ ይገኛል" ብለዋል፡፡  

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተወካይ አቶ አዝመራው ተዘራ በበኩላቸው የላይአርማጭሆ ህዝብ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የህዝብ መከታና አለኝታ ለሆነው የመከላከያ ሰራዊት አጋርነቱንና ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር ያስመሰከረበት ነው ብለዋል፡፡

ሽብርተኛው ህወሃት ሁለቱን ህዝቦች በመከፋፋልና በማጋጨት አማራውን ለማዳከም ድብቅ ሴራውን ሲያራምድ መቆየቱን ጠቁመው "ዛሬ ላይ ሁለቱ ህዝቦች አንድነታቸውን በጋራ በማጠናከር ወራሪውን ለመፋለምና ለመደምሰስ ግንባር ፈጥረው እየታገሉ ናቸው" ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት  በሁለቱ ህዝቦች መካከል ጥላቻና ጥል እንዲፈጠር  ለረጅም ጊዜ  ከሰራው የፖለቲካ ሴራ በመላቀቅ የጀመሩት የትብብርና የደጀንነት እንቅስቃሴ ተጠናከሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የቅማንት ተወላጆቹ ለሰራዊቱ 20 ሙክት በጎች፣  20 ኩንታል ቆሎ፣ አምስት ኩንታል ስኳር፣ ሁለት ኩንታል ደረቅ ሬሽንና 20 ጥንድ አንሶላ በድጋፍ  አበርክተዋል፡፡

በድጋፍ አሰጣጥ ስነ-ስርአቱ ላይ የወረዳው ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የጎንደር ከተማ አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም