ቀጥታ፡

ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እና ያልተገባ ጫና የሚቃወም ሰልፍ ነገ በብራሰልስ ይካሄዳል

ህዳር 5/2014 (ኢዜአ) የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እና ያልተገባ ጫና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ነገ በቤልጂየም ብራሰልስ ከተማ ይካሄዳል።

ሕዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄደው ሰልፍ በአውሮፓ ኮሚሽን (European Commission) ፊት ለፊት በኢትዮጵያውያን ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 10 ሰአት እስከ 12 ሰአት እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበራት በቤልጂየም አስተባባሪ አቶ ዘሪሁን አሰፋ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት ለመቃወም የሚካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል።

"ምዕራባውያን አገራት ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ"፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጩትን የሐሰት መረጃ ያቁሙ፣ እኛ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጎን ነን" የሚሉ እና ሌሎች ተጓዳኝ መልዕክቶች ይተላለፋሉ ብለዋል።-896+

ለአገር መከላከያ ሰራዊት እና በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በግፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰልፈኞቹ ያላቸውን ድጋፍ እና አጋርነት እንደሚገልጹም አመልክተዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች እየፈመ ያለውን ግድያ፣ የንብረት ማጥፋት እና ሕዝብ የማፈናቀል እንደሚያወግዙም ነው አቶ ዘሪሁን የገለጹት።

ለአውሮፓ ሕብረት፣ ለአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት፣ ለአውሮፓ ኮሚሽን እና ሌሎች በሕብረቱ ስር የሚገኙ ተቋማት ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ እና አድሏዊ ምልከታቸውን እንዲያቆሙ የሚያሳስብ ደብዳቤ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአውሮፓ ሕብረት እና በስሩ ለሚገኙ ተቋማት ሃላፊዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ቤልጂየም፣ ጣልያን እና ኔዘርላንድ ጨምሮ በስምንት የአውሮፓ አገራት የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።

"ሰልፉ በውጭ የሚኖረው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በፖለቲካ እና በአመለካከት ልዩነቶች ቢኖሩትም በኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ እንደሆነና በአገሩ ጉዳይ እንደማይደራደር የሚያሳይበት ነው" ብለዋል አቶ ዘሪሁን።

ዳያስፖራው የምዕራባውያን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበልና እንደማይታገስ የሚገልጽበት እንደሆነም ገልጸዋል።

በቤልጂየም የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለኢትዮጵያ ሕልውና እና ሉዓላዊነት መጠበቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አክለዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም