ቀጥታ፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፋጣኝ ውሳኔዎችን ወስዶ ውጤታማ ግዳጅ ለመፈጸም ዕድል የሚሰጥ ነው

ህዳር 5/2014 (ኢዜአ) አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፋጣኝ ውሳኔዎችን በመውሰድ ውጤታማ ግዳጅ ለመፈጸም ዕድል የሚሰጥ መሆኑን የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ተናገሩ።

የቀድሞው ገነት ጦር ትምህርት ቤት ምሩቃኑ ብርጋዴር ጀኔራል ሰብስቤ ንጋቱ እና ኮሎኔል ገበየሁ አበበ በቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የጦር መኮንኖች ናቸው።

መኮንኖቹ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሶማሊያ ወረራ ብሎም በሰሜን ኢትዮጵያ የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ተጋድሎ ውጤታማ ግዳጆች የፈጸሙና አገራቸውን በተለያዩ ሃላፊነቶች ያገለገሉ የአገር ባለውለታዎች ናቸው።

በየዘመኑ ከጠላት ጋር ይወግኑ የነበሩ ካሃዲዎች ነበሩ ያሉት መኮንኖቹ ጥቅምት 24 ቀን 2013 አሸባሪው ህወሃት በሰራዊቱ የሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው ጭካኔ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም ብለዋለ።

ድርጊቱ ወደር የማይገኝለት የከሃዲዎች የአረመኔነት መገለጫ እንደሆነ ገልጸው፤ ኢትዮጵያዊያን ከሃዲዎችን ግንባር ድረስ ከመዋጋት በተጨማሪ ሰርገው በመግባት የአሸባሪውን ተልእኮ የሚያስፈፅሙ ተላላኪዎችን ተደራጅተው መመከት አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ በግልጽ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የሕወሃት ወራሪ ሃይል ለትግራይም ሆነ ለማንኛውም ህዝብ የማይጠቅም ከሃዲ ቡድን መሆኑንም ከፍተኛ መኮንኖቹ ጠቅሰዋል።

በቅርቡ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኢትዮጵያ ያጋጠማት የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ወሳኝ እንደሆነም አብራርተዋል።

በአዋጁ ከጥፋት ቡድኑ ጋር በግልጽና በስውር የሚሰሩ ባንዳዎችን እየመረመረ እርምጃ የሚወስድበት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ አፋጣኝ ውሳኔዎችን በማራመድ ግዳጁን ለማፋጠን እንደሚያስችለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም