ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በፈተናዎች ውስጥ እንደወርቅ እየነጠረ የመጣ እንጂ በምዕራባዊያን በሬ ወለደ ዜና የሚሸበር አይደለም

አርባምንጭ ህዳር 4/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ በፈተናዎች ውስጥ እንደወርቅ እየነጠረ የመጣ እንጂ በምዕራባውያን በሬ ወለደ ዜና የሚሸበር አለመሆኑን የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ወልደገብርኤል ላቀው እንዳለው ሲኤንኤን፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ፍራንስ 24 እና መሰል የምዕራባውያን ሚዲያ ተቋማት የኢትዮጵያን ቀውስ ለማባባስ ሆን ዘመቻ ከፍተዋል።

እነዚህ የምዕራባውያን ሚዲያ ተቋማት እያሰራጩት ያለው ዘገባ ከጋዜጠኝነት መርሆ አንጻር ተጨባጭነትና ሚዛናዊነት የጎደላቸው እንዲሁም አድሏዊ ነው ብለዋል።

ጋዜጠኛው እንዳለው ሰሞኑን አዲስ አበባ በህወሓት ታጣቂዎች ተከባለች ብለው አይን ያወጣ የሀሰት ዜና መልቀቃቸው አስነዋሪ ተግባር ነው።

ስለመገናኛ ብዙሃን ስነ-ምግባርና መርሆ ይናገራሉ እንጂ አይተገብሩትም ብሏል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ስርዕት ግንባታ ኢትዮጵያ አንጸባራቂ ለውጥ እያሳየች መምጣቷ አንዳንድ ምዕራባዊያን መንግሥታትን እያንገበገባቸው ነው።

የእነዚህን መንግሥታት እኩይ ተግባር ኢትዮጵያውያን በትዊተር እየተፋለሙ የዜግነት ድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ጠቅሷል፡፡

የአሸባሪው ህወሓት የጥቅም ተጋሪ የሆኑ እነዚህ ሚዲያዎች የሚያሰራጩትን የተዛባ ዘገባ ለማጋለጥ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስቧዋል።

ጋዜጠኛ ጩባ ጭኖ በበኩሉ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ ካላቸው የተንሸዋረረ አመለካከት በመነሳት የሀገራችን ገፅታ ለማጠልሸት ሆን ብለው የሚዲያ ጦርነት መክፈታቸውን ገልጸዋል።

በጋዜጠኝነት ስነ-ምግባርና መርሆ አንፃር ተጨባጭነት የሌለው የፈጠራ ዜና ማሰራጨት በህግ እንደሚያስጠይቅ ጠቅሶ ምዕራባውያን ሚዲያን ለእኩይ ተግባር በማዋል ሙያውን እያራከሱ ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጠውን መንግሥትን እጅ በመጠምዘዝ ህወሓትን ወደ ስልጣን ለማምጣት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለም ጠቅሷል።

የእነዚህን ሚዲያዎች እኩይ ተግባር ከመመከት አንጻር ከመገናኛ ብዙሀን ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቅሶ የተዛቡ ዘገባዎችን በማጋለጥ የድርሻውን እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግሯል።

ምዕራባውያን በሀገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የበርካታ ሀገሮችን ሰላምና ደህንነት ስማገታቸው የአፍጋኒስታን፣ የሊቢያና የሶሪያ ቀውስ ህያው ምስክሮች መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በፈተናዎች ውስጥ እንደወርቅ እየነጠረ የመጣ እንጂ በምዕራባውያን በሬ ወለደ ዜናዎች የሚሸበር አይደለም ብሏል፡፡

የጋሞ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ያዕቆብ ጌጃ በበኩላቸው የኢትዮጵያን መንግሥት እጅ በመጠምዘዝ ከአሸባሪዎች ጋር ድርድር እንዲደረግ አቅደው ዘመቻውን እንደጀመሩት ገልጸዋል።

ይህ ዘመቻ እውነትን መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ እንደማይሳካላቸው አረጋግጠው በማህበራዊ ድረገጽ በመጠቀም የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የምዕራባውያንን እርባና የሌላቸውንና ምንጭ አልባ ዘገባዎችን በማጋለጥ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም