የኢትዮጵያና ኤርትራ ኮሚዩኒቲ የህዝብ ለህዝብ የጋራ ውይይት ዶሃ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ኤርትራ ኮሚዩኒቲ የህዝብ ለህዝብ የጋራ ውይይት ዶሃ ተካሄደ
አዲስ አበባ ነሃሴ 14/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ ኮሚዩኒቲ የህዝብ ለህዝብ የጋራ ውይይት በኳታር ርዕሰ መዲና ዶሃ ተካሄዷል። በኳታር ዶሃ የሚኖሩ የኢትዮጵያና ኤርትራ ኮሚዩኒቲ አባላት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን እርቅና ሰላም ምክንያት በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት የጋራ ስብሰባ ባሳለፍነው ሳምንት ማካሄዳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር መታሰቢያ ታደሰ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በሁለቱ ሀገራት የተጀመረውን የእርቅ ሂደት የበለጠ ለማጠናከር የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ብለዋል። እርቁ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያለው ፋይዳ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ሲሉም አምባሳደር መታሰቢያ አክለው ተናግረዋል። በኳታር የኤርትራ አምባሳደር ዓሊ ኢብራሂም አህመድ በበኩላቸው የተፈጠረው ሰላምና እርቅ ሁለቱ ህዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፍ ላይ መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ለቀጠናው በሙሉ ትልቅ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ማስታወቃቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።