ቀጥታ፡

የህወሓት የጥፋት ዓላማ ፈጻሚዎች በምዕራብ ጎንደር ዞን በኩል ከሱዳን ሰርገው እንዳይገቡ ዝግጅት ተደርጓል

መተማ፣ ህዳር 4/2014 (ኢዜአ )የህወሓት የጥፋት ዓላማ ፈጻሚዎች በምዕራብ ጎንደር ዞን በኩል ከሱዳን ሰርገው እንዳይገቡ ከገቡም ለመደምሰስ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የዞኑ የህዝብ ሰላምና ደህንነት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር አሰፋ ሸቤ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ከዚህ በፊት በዞኑ ተደጋጋሚ ትንኮሳ ለማድረግ ሞክሮ በጸጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት በርካታ አባላቱና ግብረ አበሮቹ ተደምስሰዋል።

ኃላፊው እንዳሉት፣ ''አሁንም መላ ህዝቡ ይህን ወራሪ ኃይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር በበቂ ዝግጅትና ቁርጠኝነት ላይ ይገኛል።'' ከሱዳን ጋር በሚዋሰኑ ሁሉም መግቢያ በሮች አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገ ነው።

"የሽብር ቡድኑ በዞኑ ጥቃት ለማድረስ ቢመጣ ራስን እንደማጥፋት ነው የሚቆጠረው" ያሉት ኮማንደሩ፣ ወራሪውን ለመቅበር የተዘጋጀ የፀጥታ ኃይልና ህዝብ አለ ብለዋል።

የክልሉን መንግስት የክተት ጥሪ በህዝባዊ ማዕበል ለመመለስ የዞኑ ህዝብ ወደ ግንባር እየተመመ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሕዝቡ ጠላትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደመቃብር ለማውረድ በቂ የስነ ልቦና ዝግጅትና ቁርጠኝነት እንዳለው ኮማንደር አሰፋ ገልጸዋል።

የዞኑ ህዝብ የሀገርን ዳር ድንበር አስከብሮ የቆየ ባለታሪክና የልማት አርበኛ መሆኑን ያስታወሱት ኮማንደሩ፣ "አሁንም አሸባሪውን በመደምሰስ ተጨማሪ ታሪክ ለመስራት ተዘጋጅቷል" ብለዋል።

የተለያዩ አደርጃጀቶችን በመፍጠር ጠላትን ሌት ተቀን በንቃት መከታተልና መደምሰስ የዞኑ ሕዝብና አመራሩ በቅንጅት እየሰሩ ነው።

ጠላት በሱዳን በኩል ሰርጎ እንዳይገባ መመከት ብቻ ሳይሆን ከገባም ተመልሶ እንዳይወጣ ለመደምሰስ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

"ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በዞኑ ሁሉም ቀበሌዎችና የከተማ አካባቢዎች ፀጉረ ልውጦችን ይዞ ወደህግ ለማቅረብ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሰርቷል።

በእዚህም ኅብረተሰቡ የ24 ሰዓት አካባቢውን በንቃት እየጠበቀና የተጠናከረ ክትትል እያደረገ  ነው።

በመተማ ወረዳ የዘባጭ ባህር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መልኬ አበበ እንዳሉት መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል ወደግዳጅ ቀጠና እየሄዱ ነው።

አክለውም ''ለሰላምና ልማት ቅድሚያ እንሰጣለን እንጂ ጦርነትን ከጠላቶቻችን በላይ እናውቃለን።'' ጠላትን ለመደምሰስ በቂ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት።

ጠላት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሸንፎ የሀገር ሰላም እስኪረጋገጥ ድረስ ከፀጥታ አካሉ ጎን ተሰልፈው ሀገርና ህዝብን ይታገላሉ።

''ሀገር ከሌለ ሰርቶ መብላት፤ ወልዶ ማሳደግም አይቻልም'' ያሉት ደግሞ ከዚሁ ቀበሌ ወደ ግንባር የተሸኙት አርሶ አደር የሺዋስ አበራ ናቸው።

በየትኛውም ጊዜና ቦታ ጠላትን በመጣበት ቦታ ለመቅበር ዝግጁ መሆናቸውንም አርሶ አደር የሺዋስ  ተናግረዋል።

አሸባሪውን ህወሓት መደምሰስ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ግዴታ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም