የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተባበሩ! - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተባበሩ!
የዚህ ጽሁፍ ባለቤት መልካሙ ዘርይሁን ኣስራት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ፋኩልቲ በፕሬስ ጋዜጠኝነት በዲፕሎማ እና በሬዲዮ ጋዜጠኝነት በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ፤ 'ንጉስ አርማህ' እና 'ህንደኬ' የተሰኙ ታላላቅ ታሪካዊ ተውኔቶችን ጽፎ ለእይታ ያበቃ እንዲሁም 'የኛ እድር' የተሰኘ ሳታየር ኮሜዲ ደርሶ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች፣ በውጭ አገር በለንደንና ዋሽንግተን ከተሞች የታየለት ታላቅ የኪነጥበብ ሰው ነው።
‘Get up stand up, stand up for your right!’
‘Buffalo soldiers’ Bob Marley
ከአምስት መቶ ዘመን በፊት የተጀመረው የጥቁር ህዝቦች መከራ ስልቱንና አቅጣጫውን እየቀያየረ አሁን ድረስ ዘልቋል፡፡ አስቀድሞ በቀጥታ በሚደረጉ ውጊያዎችና ውንብድናዎች ሰፊውን የጥቁር ማህበረሰብ ወደ ባርያ ፍንገላና አፈና ወሰዱት፡፡
በዚያን ወቅት በነበሩ አፍሪቃውያን መሪዎች የጠነከረ መከላከል ገጠመው፡፡ የኮንጎው ንጉስ ማሬምባ እ.አ.አ በ1526 ከፖርቹጋል ባሪያ ፈንጋዮች ጋር ከፍተኛ ግብግብ ገጠመው፡፡ የአሁኖቹ ቤኒን፣ ናይጄሪያ እና አንጎላም በዚህ ኢሰብአዊ የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ወገኖቻቸውን ከባሪያ ፈንጋዮች ለመታደግ የሞከሩ አፍሪካዊ አገሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የሴኔጋሉ ንጉስ አልማማይ እ.አ.አ በ1787 የባሪያ ፍንገላን ህገወጥ ያደረገ ሲሆን ከማንም አውሮጳዊ ሀገር ቀድሞ ነበር ህጉን ያወጣው፡፡
ይሄ የአፍሪካውያን የተበታተነ ተቃውሞ ለአውሮጳውያን ማፈግፈግን ሳይሆን መላቸውን ቀይረው ወደ አፍሪካ መጠጋትን መረጡ፡፡ ላያቸው በማር የተለወሱ ውስጣቸው ግን የአፍሪካን የሰው ሀይልና ተፈጥሮአዊ ሀብት መግፈፍ የሚያስችሉ ማታለያዎችን በማቅረብ ወደ መካከለኛው የአፍሪካ ክፍል ለመቆናጠጥ ቻሉ፡፡
የኛ የአፍሪካውያን ከስልጣኔ ጋር ያለን ትውውቅ አውሮጳውያን እንደሚሉት በነሱ አማካኝነት ተገለጠ ከሚሉት ዘመን አምስት መቶ ዓመት ብቻ እንደሆነ ይቆጥሩታል፡፡ ግና አፍሪካውያን ከስልጣኔ ያላቸው ትውውቅ ረዥምና ለአውሮጳው ስልጣኔ መሰረቱ የአፍሪካውያን የብዙ ሺህ ዘመን ምርምርና ውጤት መሆኑን ለመገንዘብ አልፈቀዱም፡፡
የግሪክ ፈላስፎች አርኪሜዲስና ፓይታጎረስ የሂሳብ ሊቃውንት የሆኑት ወደ ግብጽ ዘልቀው በአፍሪካውያን፣ ኑብያውያን የሂሳብ ጠቢባን ከሺህ ዘመን በፊት የቀመሩትን መጽሀፍት አገላብጠው እንደነበር ራሳቸው ግሪኮችም አልካዱም፡፡
የኢትዮጵያውያን፣ የኑብያውያን የስነ-ፈለክ ምርምሮችና የሺህ ዘመን ጥንቅሮች አሁንም ለዘመናዊው ዓለም ስነ-ከዋክብት ጥናት መሰረቶች ናቸው፡፡
ታላቁ እስክንድር ዓለምን በሀይል ለማስገበር በነበረው ጉጉት ግብጽን በተቆጣጠረ ወቅት በግብጽ ከተሞች ውበትና ጽዳት፣ በህዝቡ ስልጡንነት ተደምሟል፡፡ ከቶም በሀገሩ ግሪክ የሌለው ስልጣኔ በያኔዋ ጥቁር ግብጽ ማግኘቱ የታሪክ መዛግብቱ ውስጥ ተጽፏል፡፡ እናም ቀድሞ ያደረገው ነገር ቢኖር ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የነበረውን የጥቁር ህዝቦች አንጡራ ሀብት የሆኑትን በብራና በሄሮግሎፊክስ የተጻፉትን እውቀቶች አነደዳቸው፡፡ የእስክንድር ዜና መዋእል እንደሚጠቁመው እኒያን የሰው ልጆች ከምድር ጋር ከተዋወቁ ዘመን ጀምሮ የዳጎሱዋቸውን መዛግብት የእሳት እራት አደረጋቸው፡፡
በግብጽ ቤተ-መዛግብት ውስጥ ያገኛቸውን እኒያን ብርቅ የጥቁር ህዝቦች የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የሳይንስ እንዲሁም የስነፈለክ ጥርቅሞችን አንድዶ ለመጨረስ ስድስት ወር ፈጀበት፡፡
ወደ ሜሶፖታሚያና ፋርስ በዘለቀ ግዜም እዚያም ቤተ-መዘክሮቻቸውን ቢያገላብጥ የጥቁር ህዝቦች መሰረት መኖሩን በተገነዘበ ግዜ በግብጽ እንዳደረገው ሁሉ ከተሞቻቸውን፣ ሀገራቱንና መዘክሮቻቸውን አመድ አደረገው፡፡
የሱን ፈለግ የተከተሉት ነጭ ወራሪዎች ባገኙት፣ በገቡበት ሁሉ የጥቁርን ስልጣኔና ስልጡንነት የሚገልጹ ቅንጣጢቶች ሳይቀሩ አወደሙ ያልቻሉትን ወደ አውሮጳ ይዘው ሄዱ፡፡ የአክሱም ሀውልትን ጉዞና መልስ ማስታወስ ጉዳዩን በሚገባ ለማስረዳት ይቻላል፡፡
በቅርቡ እንኳ ከቤኒን የተጋዙ ቅርሶችን ጀርመን ከሙዚየሞቿ ሰብስባ ለመስጠት መወሰኗን ሰምተናል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘው አንድ አፍሪካዊ ምሁር እንደተናገሩት፤ በአውሮጳ ሙዝየሞች ያሉ የአፍሪካ ቅርሶች ሁሉ ቢመለሱ ሙዝየሞቹ ጎብኚ አጥተው ይዘጉ ነበር ነው፡፡
ጀነራል ናፒየር አፄ ቴዎድሮስን ከወጋ በኋላ ይዞት የተመለሰው ቅርስ አሁንም ድረስ የለንደንንና የፓሪስን ሙዝየሞች እንዳጨናነቁ እናውቃለን፡፡
ከኋላ የመጣ አይን አወጣ ካልሆነ በቀር ከቶም አውሮጳ አፍሪካውያንን ሊያሰለጥኑ እንደማይችሉ እነሱም ያውቃሉ፣ እኛው ይገባናል፡፡
ሌላው በመርዝ ተለውሶ ወደ አፍሪካ የቀረበው ደግሞ ሀይማኖት ነበር፡፡
ጥንታዊው የይሁድ ሀይማኖት በያእቆብ ዘመን ተሰዶ የመጣው ወደ ጥቁር ግብጽ ነበር፡፡ ሀይማኖቱ አድጎ ፋፍቶ በሙሴ መሪነት ከስድስት መቶ ዘመን ቆይታ በኋላ ወደ ከነዓን ሲመለስ ሰባት ሆነው መጥተው በብዙ እልፍ በዝተው በሙሴ መሪነት እንደገና ወደ ከነዓን ሄደው ሲቋቋሙ የጥቁር አፍሪካውያን ውለታ በሚገባ ማስታውስ በተገባቸው ነበር፡፡
ሁለቱ ታላላቅ የዓለም ሀይማኖቶች እስልምናና ክርስትና አውሮጳውያን በቅጡ እምነት ሳይገባቸው፣ አፍሪካውያን ቤተ-ክርስቲያን ሆነ መስጊዶችን ገንብተው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ፈጣሪያቸውን ሲያመልኩ እንደነበር ምስክር መጥራት አያሻም፡፡
ኢትዮጵያዊው የንግስት ሕንደኬ ጃንደረባ ኢየሩሳሌም ወርዶ በዮርዳኖስ ወንዝ ውሀ በፊሊጶስ እጅ ተጠምቆ ክርስትናን እንደተቀበለ መጽሀፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡
በእስልምና ታሪክ ውስጥም የመጀመሪያው ሂጅራ (እስላማዊ ቅዱስ ስደት) የተደረገው ወደ አፍሪካ ነው፡፡ ወደ አክሱም፡፡ የመጀመሪያው ሙአዚን አፍሪካዊው ቢላል ነው፡፡
ታዋቂው የኬንያ እንዲሁም የአፍሪካ የነጻነት አባት ጆሞ ኬንያታ ሀይማኖትን አስመልክተው ከሚጠቀሱት ዝነኛ ንግግሮቻቸው መካከል ‹‹ለኛ ለአፍሪካውያን መጽሀፍ ቅዱስን ሰጥተውን አጎንብሳችሁ አንብቡ ብለውን እነሱ ግን በኛ ትከሻ ላይ አሻግረው መሬታችንን ይማትራሉ›› እንዳሉት ነው የሆነው፡፡
አውሮጳውያን ያስተማሩን ያሳወቁን ሀይማኖት የትኛውን ነው? ያስተዋወቁን አምላክስ ማንን ነው? የአውሮጳውያን ስልጣኔና ሀይማኖት ትሩፋቶች ታዲያ ምንድናቸው?
መልሱ ቀዳሚው ትሩፋት ረሀብ ነው፡፡ አውሮጳውያን እግራቸውን ወደ አፍሪካ ከመምጣታቸው ቀድሞ አፍሪካ በረሀብ የሚታወቅ ከባቢ አልነበረም፡፡ ራሳቸው አውሮጳውያን ሆነ መካከለኛ ምስራቅ በረሀብ ሲጠቃ በውሀ ጥም ሲቃጠል፣ ረሀቡንም ሆነ ውሀ ጥሙን የሚከላከለው ወደ አፍሪካ በመዝለቅ የዓባይ ውሃን በመጎንጨት ነበር፡፡
መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚነግረን በከነዓን የተነሳው ድርቅ በጎቻቸውንና ራሳቸውን እረኞቹን እስራኤላውያን ሲፈጃቸው በሀብት ወደ ተትረፈረፈችው ጥቁር ግብጽ ነበር ጎራ ያሉት፡፡
ሌላው ከአውሮጳውያን የስልጣኔና የሀይማኖት አስተምህሮ የተረፈን ደግሞ ጦርነት ነው፡፡ ይሄ የአውሮጳ ስልጣኔ ቅርስ የጥይት አረር ያልጨሰበት የአፍሪካ ምድር ማግኘት እስኪከብድ ድረስ እርስ በርሳችን፣ ከጎረቤቶቻችን ጋር ከራሳቸው ከአውሮጳውያን ጋር ባለፉት አምስት መቶ ዘመናት ተዋግተናል፤ ተራርደናል አሁንም አውሮጳ ሰራሽ ቅንቡላዎችን፣ ሚሳይሎችን የቡሄ ጅራፍ ያህል እንዣለጥበታለን፡፡
ሰላም ማጣታችን ደግሞ ሌላው ከአውሮጳውያን የተቀበልነው ጉድ ነው፡፡ አሁን አሁንማ በታሪክ ስንሰማው እንደነበረው በአፍሪካ የነጻነት ዘመን ማግስት በስድሳዎቹ አመታት በባሰ በአፍሪካ መፈንቅለ መንግስት እንደ ሰደድ እሳት ተያይዞ በመንደድ ላይ ይገኛል፡፡
በዴሞክራሲያዊ መንገድ መመረጥ አንድን የአፍሪካ መሪ በወታደር አሊያም በአውሮጳውያን ጣልቃ ገብነት መውደቁ አይቀርም፡፡ መሪው የአይኑ ቀለም ካላማራቸው ተባብረው እንደ ገና ከብት ይዘረጥጡታል፡፡ በተለይ በተለይ አፍሪካን ለማስተባበር የፈቀደ መሪ ወዮ ለሱና ለህዝቡ፡፡
ታዋቂው አሜሪካዊው የኤፍቢአይ (F.B.I) መስራችና የረዥም ዘመን ዳይሬክተር ኤድጋርድ ሁቨር ለአሜሪካን ከፍተኛ ስጋት ምንድነው ብለው ጋዜጠኞች ሲጠይቁት የኔግሮዎች ወይም የጥቁሮች ህብረት ነው፡፡ ብሎ እቅጩን ተናግሮ ነበር፡፡
ይሄው የአሜሪካ የሰላዮች አለቃ ራሱ ቅድመ አያቱ ጥቁር እንደነበረችና ይሄን እውነት የሚያውቁት ጥቁር ዘመዶቹ ትንፍሽ ቢሉ ፈጥርቆ እንደሚገላቸው አስፈራርቶ ዝም አሰኛቸው፡፡ እሱ ግን በአሜሪካን የተነሱትን ሁሉንም የጥቁር ነፃነት ትግሎችን በቀጥታ በሚያደርገው መንግስታዊ ግድያና ተዘዋዋሪ ግድያ ትግሉን አኮላሸው፡፡
ማልኮም ኤክስና ማርቲን ሉተር ኪንግን በጠራራ ፀሀይ ሲያስደፋቸው፣ ተከታዮቻቸውን ደግሞ በወረንጦ ለቅሞ ፈጃቸው፡፡ ብላክ ፖንዘር በመባል የሚታወቁትን የጥቁር መብት ታጋዮችን ደግሞ ኮሚኒስቶች ናቸው በሚል እንደትንኝ አሽቶ አድፈጠፈጣቸው፡፡ ለግዜውም ቢሆን የጥቁሮችን ድምፅ አዳፈነው፡፡
አሁን በኢትዮጵያውያን ላይ አሮጌው የነጭ ብትር እየተሰነዘረ ይገኛል፡፡ አሸባሪውን ህወሃትን ተገን አድርጎ የመጣው የአውሮጳውያን ንክሻ ተላላኪውን ህወሃትን በመንቀልና የአሜሪካን የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ተጽእኖ ተቋቁሞ ይሄን ጊዜ መሻገር እንደምንችል መላ ኢትዮጵያውያን አንጠራጠርም፤ ግን ከዚህ ትግል ጎን መላው የጥቁር ህዝብ ከጎናችን እንዲሰለፍ የምናደርግበትን ወርቃማ እድል እንዲያመልጠን ማድረግ አይገባም፡፡ መላ የጥቁር ህዝቦች ከወንድሞቻቸው ኢትዮጵያውያን ዙርያ ገብ እንዲሰለፉ ማድረግ ይገባናል፡፡
የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል፣ የጥቁር ህዝቦች አርማ ወደ ሆነችው ሀገራቸው ኢትዮጵያ የአውሮጳውያን የረሀብ፣ የጦርነትና የሰላም ማጣት መርከብ በመቅዘፍ ላይ ይገኛል፡፡ ይህን መርከብ መላ ጥቁር አፍሪካውያን፣ ጥቁር አሜሪካውያን መላ ሰላም ወዳድ የዓለም ህዝቦች ተባብረን ዳግም ላይመለስ መርከቢቱን ውቅያኖስ ስር ልናስምጣት ይገባል፡፡