ቀጥታ፡

ለሠራዊቱ ስንቅ ከማዘጋጀት ባሻገር ሌሎች አገራዊ ግዴታዎችን ለመወጣት ዝግጁ ነን

ህዳር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለአገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ ከማዘጋጀት ባሻገር የሚጠበቅባቸውን ሌሎች አገራዊ ግዴታዎችን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የአራዳ ክፍለ ከተማ ሴቶች ገለጹ፡፡

የክፍለከተማው አስተዳደርና የእናት አገር ጥሪ ኮሚቴዎች ባስተባበሩት የደረቅ ስንቅ ዝግጅት የክፍለ ከተማው ነዋሪዎችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ለሠራዊቱ የሚሆን የደረቅ ምግቦች ስንቅ የማዘጋጀት ሥራ በይፋ ተጀምሯል፡፡

በስንቅ ዝግጅቱ የተሳተፉ ሴቶች ከስንቅ ዝግጅት ባለፈ የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ግዴታ ለመወጣት ያላቸውን ተነሳሽነት ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ደጀንነት ለመግለጽ በስንቅ ዝግጅቱ በመሳተፋቸው ደስተኞች መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

"የመዲናዋ ነዋሪዎች የአካባቢያችንን ሠላም  በመጠበቅ አገራዊ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል" ሲሉም አክለዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ "አባወይ ዮሐንስ አገር በአሸባሪው ኃይል የገጠማትን ተግዳሮት ለማለፍ  ሁሉም በአቅሙ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡

ስንቅ  የማዘጋጀቱ ተግባር  ክፍለ ከተማው ከእናት አገር ጥሪ ኮሚቴዎች  ጋር  በመቀናጀት  ማስጀመሩን ገልጸዋል።

ከስንቅ ዝግጅቱ በተጨማሪ ባለፉት አምስት ቀናት 39 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት ለመከላከያ ሠራዊት ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ፤ ሕዝቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም