ቀጥታ፡

የመዲናዋን ሰላም ለማስጠበቅ ከ27 ሺህ በላይ ወጣቶች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመዲናዋን ሰላም ለማስጠበቅ ከ27 ሺህ በላይ በጎፈቃደኛ ወጣቶች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ "በመረረ ትግላችን ጣፋጭ ድል እናጣጥማለን" በሚል መሪ ሐሳብ ወጣቶች የውይይት መድረክ አካሄዷል፡፡

በመድረኩም ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ2ሺህ በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ፤ የከተማዋ ወጣቶች የአከባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ ከ27 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተደራጀ መልኩ የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል፤ ለሰራዊቱን በገንዘብና ቁሳቁስ በመደገፍ  እንዲሁም ደም በመለገስ የሚያኮራ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሰራዊቱን ለማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ እና የውጭ ጫናን ለመመከት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥበቡ በቀለ፤ አሸባሪዎቹ የህወሓትና ሸኔ ቡድኖች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ቅንጅት ፈጥረው እየሰሩ መሆናቸውን ለውይይቱ የመነሻ ጹሑፍ ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኖቹም አገርን ለማፍረስ የያዙትን ዓላማ ለማሳካት የአንድ ወገን ተቆርቋሪ በመምሰል በሌላው ወገን ላይ የጭካኔ በትር በማሳረፍ ንጹሃን ዜጎችን እንደሚጨፈጭፉ ተናግረዋል።

የውጭ ታሪካዊ ጠላት የሆኑት ግብጽና ሱዳንም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ሽብርተኛ የሆኑትን የህወሓት፣ ሸኔና መሰል የጉምዝ ታጣቂዎችን በማሰማራት ግጭትና አለመረጋጋት እንዲባባስ እያደረጉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ጦር የመዘዙባትን ኃይሎች በመመከት ጦርነቱን መቋጨት፣ የምዕራባዊያንን ጫና በአንድነት መመከትና ሽብርተኛ ኃይሎችን ማጥፋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሽብር ቡድኑን የጥፋት እግሮች ማሳጠርም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገትና ሉዓላዊነቷን ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር አስፋው ተክሌ በበኩላቸው፤ ወጣቶች የጀመሩትን የሰላም ሥራ አጠናክረው በማስቀጠል የአገራቸውን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘመን የገጠሟትን ጠላቶች አሳፍራ በነጻነት የቆመች ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የውስጥና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያከናውኑት ሴራ ፈጽሞ አእንደማይሳካም ነው ያነሱት፡፡

የመዲናዋ ወጣቶች ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና መንግሥታዊ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረቡት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበረሰብ ዓቀፍ ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር ሰለሞን ፋንታሁን ናቸው፡፡

አሁን የተጀመሩት አበረታች ሥራዎችን በጠንካራ አደረጃጀት በመደገፍ ቀጣይነት ያለው የሰላምና ደህንነት ግንባታ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

በከተማዋ በበጎ ፈቃድ የሰላምና ደህንነት ሥራ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በመረዳት ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የሐሰት መረጃ፣ ህገ-ወጥ ግብይት እና ሌሎች ያልተገቡ ድርጊቶችን  እየፈጸሙ አካላትን ለጸጥታ ኃይሉ መጠቆም እንደሚገባም አመላክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች የጀመሩትን የሰላምና ደህንነት ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመድረኩ አረጋግጠዋል።

አሸባሪው የህወሓት ኃይል ለሽብር ተግባሩ ይጠቅሙኛል ያላቸውን ኃይሎች በማሰባሰብ ጦርነት ቢከፍትም ኢትዮጵያ የማሸነፏ ነገር ግን እርግጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

በቀጣይም የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ የአገር መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል ጨምሮ እስከ ግንባር ድረስ በመሄድ ለሠራዊቱ የሚያደርጉትን ደጀንነት እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።

"ኢትዮጵን ካላፈርስን እንቅልፍ አንተኛም" ያሉ የሽብር ቡድኖችን እና የዓለም አቀፍ ጫናዎችን በአንድነት በመመከት የአገራቸውን ሉዓላዊነት እንደሚያስቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም