የግብጽ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ግጭት አባባሽ ዘገባዎችን እየሰሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብጽ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ግጭት አባባሽ ዘገባዎችን እየሰሩ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) አንዳንድ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በማባባስ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል እየሰሩ መሆኑን የዓረብ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኞች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የዓረብ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኞች እንደገለጹት፤ አንዳንድ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማባባስ እየሰሩ ነው።
ይህንንም የሚያደርጉት የኢትዮጵያን የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት ደኅንነት በማወክ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል በማሰብ መሆኑን ነው ተንታኞቹ ያስረዱት።
በአሜሪካ የሚገኘው የ"ናይል ኪንግስ" ቴሌቪዥን ጣቢያ ኃላፊና ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚሟገተው ኡስታዝ ጀማል በሽር "የግብጽ መገናኛ ብዙኃን በተለይም አል-አህራምና ዴይሊ ኒውስ ኢጂፕት ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚሉ ዜናዎችን በቀን በአማካይ አምስት ጊዜ ይሰራሉ" ብሏል።
በእነዚህ መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ ዘገባዎች በአብዛኛው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ግጭት ላይ ያተኮሩና ሐሰተኛ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱ፤ ኢትዮጵያን "ለመፍረስ" የተቃረበች አገር አድርገው የሚገልጹ እንደሆኑም ተናግሯል።
በግብጽ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የምዕራባዊያን አገራት በተለይም የአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ መሆኑን አመልክቷል።
አሜሪካ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የግብጽን አቋም እንደምትደግፍና በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ወታደራዊ ድጋፍ እያደረገች እንደሆነም ጠቅሷል።
"በዓለም ፖለቲካ ያለ ጥቅም በነጻ የሚገኝ ነገር የለም፤ አሜሪካ ከግብጽ ጋር ያላትን ግንኙነት የምትፈልገው ለራሷ ብሔራዊ ጥቅም ስትል ነው፤ በዚህም በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ፍላጎት ታስጠብቃለች" ነው ያለው ኡስታዝ ጀማል።
የመካከለኛው ምስራቅ የትኛውም የፖለቲካ ኹነት የግብጽ ጣልቃ ገብነት ያለበት እንደሆነና ከዚህም አኳያ ግብጽ ከአሜሪካ የምታገኘው እርዳታ የጥቅም ምላሽ መሆኑን ጠቁሟል።
በዚህ ረገድ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ እየሰሩ ያሉት ዘገባ የግብጽና የአሜሪካ ትብብር አካል እንደሆነም አመልክቷል።
የግብጽ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማባባስ የሚፈልጉበት ሌላ ዓላማ አለ የሚለው ኡስታዝ ጀማል ይህም "በኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ደህንነት አለመረጋጋት በመፍጠር የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ማስተጓጎልን ታሳቢ ያደረገ ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያና የዓረብ አገራት ግንኙነቶች ባለሙያ ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው በአንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት አሜሪካን ጨምሮ እንዲሁም የግብጽ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት የሐሰት መረጃ ዘመቻ ዓላማ የኢትዮጵያን ስም ማጠልሸትና ቀውስ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሐብት እንዳትጠቀምና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን እንዲስተጓጎል ማድረግ መሆኑን ገልጸው፤ የምዕራባዊያንም ጫና በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከሕዳሴ ግድቡ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶችን መፍታት የምትችለው ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ በመሥራትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ስትንቀሳቀስ ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አለመረጋጋት በቀጠናው እና በመካከለኛው ምስራቅ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ የከፋ ነው ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ይህን በመረዳት ለኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለበት አመልክተዋል።