ቀጥታ፡

አፍሪካውያን የውጭ ተጽዕኖዎችን በጋራ በመመከት ጠንካራ አህጉር ለመገንባት ቁርጠኛ መሆን አለባቸው

ህዳር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) አፍሪካውያን የውጭ ተጽዕኖዎችን በጋራ በመመከት በኢኮኖሚ ራሷን የቻለች ጠንካራ አህጉር ለመገንባት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ገለጹ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም መልማት እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑንም ምሁራኑ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ እንዳሉት፤ ምዕራባዊያን አፍሪካ ላይ ጫና በመፍጠር ጥቅማቸውን ለማስከበር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

እርዳታና ብድር መከልከል ደግሞ ምዕራባውያኑ የአፍሪካ አገራትን እጅ ለመጠምዘዝ የሚጠቀሙበት ዋነኛ ዘዴ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ምእራባውያን በተለይ ዋነኛ የንግድ መተላላፊያ መስመር በሆነው የቀይ ባህር ኮሪደር ጠንካራ አገርም ሆነ መንግስት እንዲፈጠር እንደማይፈልጉ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አብራርተዋል።

በቀይ ባህር ቀጠና ያሉ አገራት ህብረት እንዲፈጥሩ እንደማይፈልጉም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ኤሲያ ጥናትና ምርምር ተቋም መምህር ዶክተር መሀመድ ሐሰን በበኩላቸው ምዕራባውያን በኢትዮጵያ መሪነት በምስራቅ አፍሪካ እየመጣ ያለውን ትብብር እንደማይፈልጉት ገልጸዋል።

 "በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው የተቀናጀ የውጭ ተጽዕኖ ደግሞ ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የምታራምደው የወንድማማችነት አካሄድ በአንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት ጥርስ እንድትገባ ማድረጉንም ነው ዶክተር መሀመድ የተናገሩት፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም እየገነቡት ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ አፍሪካ የማንንም እርዳታ ሳትሻ በራሷ አቅም መልማት እንደምትችል ትምህርት የሰጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከርና ችግሮቻቸውን በመፍታት የምዕራባውያንን ጫና መመከት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

ምዕራባውያን አፍሪካን ለጥቅማቸው እንደሚፈልጓት የሚገልጹት ምሁራኑ፤ ከዚህ አኳያ አፍሪካውያን በየትኛውም ሀገር ላይ የሚደረግ የውጭ ጫናን በጋራ በመመከት ጠንካራ አህጉር የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ አፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ አህጉር እንድትሆን የሚያስችሉ ዘዴዎቸን ቀይሶ መንቀሳቀስ እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

የአፍሪካውያን ምሁራን የአፍሪካን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና መጫዎት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም