አሜሪካ በኤርትራ ላይ ማእቀብ ስትጥል ቅድመ ሁኔታዎችን ግምት ውሥጥ አላስገባችም - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ በኤርትራ ላይ ማእቀብ ስትጥል ቅድመ ሁኔታዎችን ግምት ውሥጥ አላስገባችም
ህዳር 4/2014 የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ መንግስት አሜሪካ በትናንትናው ዕለት በኤርትራ ላይ የጣለችውን ማእቀብ አውግዟል ፤የአሜሪካ መንግስት ማእቀቡን ሲጥል ግምት ውስጥ ያላስገባቸውን ጉዳዮች እንዳሉም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ መንግስትም የሚከተሉትን እውነታዎች ከግምት ውስጥ እንዲያስገባ መንግስት ጠይቋል
1.አሸባሪው ህወሃት እኤአ ህዳር 3/2020 በሰሜን እዝ ላይ የሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ በተመሳሳይ በሉአላዊት ሃገር ኤርትራም ላይም ሮኬት አስወንጭፏል፡፡
2. የኤርትራ መንግስትም በተቃጣበት አደገኛ ሙከራ እንደ ሉአላዊ ሃገር የግዛት አንድነቱንና ደህንነቱን የማስከበር መብት አለው፡፡
3. የኤርትራ መንግስት የራሱን የግዛት አንድነት ለማስከበር የሚወስደውን እርምጃ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ያቀረበው ቅሬታ የለም፤ ጉዳዩም ይበልጥ የሚመለከታት ከሌላ ሃገር ይልቅ ኢትዮጵያን ነው፡፡
4. እ.አ.አ ሰኔ 2021 የኢትጵያ መንግስት የተናጠል የሰብአዊ የተኩስ አቁሙን ካደረገና ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ የኤርትራ መንግስትም በተመሳሳይ ሰራዊቱን አስወጥቷል፡፡
5. የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የኤርትራ መንግስት እንቅፋት ይሆናል የሚል ግምት የለውም ፤ኢትዮጵያን እና የአፍሪካ ቀንድን ሰላም እየነሳ ያለው የአሁን ግዜ አደጋ አልታረም ያለው አሸባሪው ህወሃት ነው ፤ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪውን ቡድን ጥፋት አለማውገዙ ለአሸባሪው ሃይል የልብ ልብ ሰጥቶታል፡፡
6. የማእቀቡ አላማ ነውጠኞች ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ ከሆነ አሜሪካም ሆነች አለም አቀፉ ማህበረሰብ ማእቀብና ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ያለባቸው አሸባሪው ህወሃት ላይ ነው ።
7. በመሆኑም የአሜሪካ መንግስት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማእቀብ ዳግም በማጤን ለኢትዮጵያ ሰላም ማጣት መንስኤ የሆነውን አሸባሪ ህወሃት ላይ እርምጃ እንዲወስድ የኢትዮጵያ መንግስት አሳስቧል።
አሜሪካን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሓትን የማተራመስ ሚና አለማውገዙ የሽብር ቡድኑን አበረታቶታል ብሎ መንግስት ያምናል።