ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት የሁሉም ኢትዮጵያዊ የህልውና ስጋት ነው

ህዳር 04/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያዊያን የህልውና ስጋት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በጋራ ለመከላከል በእልህ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።

አምባሳደሩ በዋሽንግተን ከስፑትኒክ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የደህንነት ስጋት የፈጠሩትን የአሸባሪው ህወሃት መሪዎች ለፍትህ ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

በውይይትና በድርድር ስም እነዚህ ግለሰቦች ከፍትህ እንዲያመልጡና አሸባሪው ድርጅትም ትንፋሽ አግኝቶ ራሱን ይበልጥ እንዲያጠናክር የሚደረገውን ሙከራ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው አጽንኦት የሰጡት አምባሳደሩ ከማንኛውም ነገር በፊት ግን አሸባሪ ቡድኑ ትጥቅ መፍታት እንዳለበት ተናግረዋል።

ለጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች ሲባል በርካታ የትግራይ ነዋሪዎች በግዳጅ የጦርነቱ ተዋናይ በመሆናቸው ጉዳቱን ከባድ እንዳደረገው ገልጸውዋል።

አሸባሪው ህወሃት ከጥቂት አምባገነን ግለሰቦች በስተቀር በየትኛውም መስፈርት የትግራይን ህዝብን ይወክላል ብለን አናምንም” ያሉት አምባሳደሩ ድርጅቱ እምነት የማይጣልበትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት እንደማይፈልግ በተደጋጋሚ ለአለም ማሳወቁንም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ የትኛውንም ዋጋ ከፍላም ቢሆን ህዝቧን ከጥቃት በመከላከል ሉአላዊነቷን እንደምታስከብር ገልጸው ሃገራቸውን ከጥቃት ለመከላከል ሲባልም በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መከላከያ ሰራዊትን በፈቃደኝነት እየተቀላቀሉ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የግዴታ የውትድርና ምልመላ ስርዓት የሌላት መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ ከሚገኙት በብዙ እጥፍ የሚበልጡት የኢትዮጵያ ወጣቶች በራሳቸው ፍላጎት በተጠባባቂነት ተመዝግበው ጥሪ እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

እነዚህ አሸባሪዎች የሁሉም ኢትዮጵያዊ የህልውና ስጋት መሆናቸውን በመረዳትም አጠቃላይ ህዝቡና ወጣቱ ለመከላከል ስራው ከፍተኛ ምላሽ መስጠቱን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት በሰሜን እዝ ላይ ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24 የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ክልሉን ከተቆጣጠረ በኋላ ለግብርና ስራና ለሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴ ሲል ለቆ ቢወጣም ቡድኑ በፈጸመው ወረራ በአፋርና በአማራ ክልሎች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዉ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም