የአዲስ አበባ ፖሊስን አዲስ የደንብ አልባሳትን አስመስሎ መጠቀም ፍፁም የተከለከለ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ፖሊስን አዲስ የደንብ አልባሳትን አስመስሎ መጠቀም ፍፁም የተከለከለ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ህዳር 04/2014 ((ኢዜአ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ነባሩን በመተካት ሥራ ላይ ያዋላቸውን ሦስት ዓይነት የደንብ አልባሳትን አስመስሎ መጠቀም ፍፁም የተከለከለ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስ ተቋማትን ለማዘመን በተያዘው ስትራቴጂካዊ እቅድ የፖሊስ ሠራዊት አርማ እና የደንብ ልብስ እንዲቀየር በተወሰነው መሰረት የአዲስ አበባ ፖሊስ አዲስ አርማና የደንብ ልብስ ስራ ላይ ማዋሉ ይታወቃል፡፡
በዚህም የአዲስ አበባ ፖሊስ ነባሩን የደንብ ልብስ በሦስት ልዩ ልዩ ዩኒፎርሞች መተካቱን ጠቁሟል፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኦሞ ሸሚዝ በጥቁር ሰማያዊ ሱሪ ከነ መለዮው፣ ካኪ ሱሪ እና ሸሚዝ በቦኔት መለዮ የደንብ ልብስን ለመደበኛ የፖሊስ ስራ እንዲሁም ቡራቡሬ ወይም ሬንጀር መልክ ያለው ለቋሚና ተወርዋሪ ኃይል የሚጠቀም መሆኑን ገልጿል፡፡
አዲስ ስራ ላይ የዋለውን ወይም ከሌሎች የፀጥታ አካላት የደንብ ልብስ ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ዩኒፎርም መጠቀም ክልክል መሆኑ በህግ የተደነገገ ስለሆነ ከአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ ጋር ተመሳሳይ ዩኒፎርም የሚጠቀሙ አካላት ማስተካከያ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ከዚህ ቀደም ሲጠቀምበት የነበረው ነባሩ የደንብ ልብስ አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑን ማስታወቁን ከተቋሙ ማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡