ቀጥታ፡

አካባቢያችንን እየጠበቅን ለህልውና ዘመቻው መስዋዕትነት ለመክፈል ተነስተናል

አሶሳ፤ ህዳር 04 / 2014 (ኢዜአ) አካባቢያቸውን እየጠበቁ ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መነሳሳታቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች አስታወቁ።

ሠራተኞቹ "የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና የመንግሥት ተቋማት" በሚል መሪ ሀሳብ  በአሶሳ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር እንዲሁም  ለአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ ተፈጻሚነት ተግተው እንደሚሰሩ ሠራተኞቹ በውይይቱ መድረክ ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ ከተሳተፉት መካከል ኮማንደር ይልማ ጥላሁን እንዳሉት አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን ለማሳካት ከመቼውም ጊዜ በላይ በማህበራዊ የትስስር ገፆች  የጥፋት ዘመቻውን ቀጥሎበታል፡፡

"የአሸባሪው ርዝራዦችም አሶሳን ጨምሮ በየአካባቢው የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እየሠሩ ነው" ብለዋል፡፡

በህወሃት   ሴራ በክልሉ መተከል እና ካማሽ የደረሰውን ሰቆቃ አንረሳውም ያሉት ኮማንደር ይልማ ፤ የበርካታ ሙያ ባለቤት የሆነው የመንግስት ሠራተኞች የቡድኑን ሃገር የማፍረስ እቅድ ለመቀልበስ  የማገዝ ግዴታ አለብን ነው ያሉት  ኮማንደር ይልማ፡፡

አካባቢያችንን ከሰርጎ ገቦች ነቅተን በመጠበቅ መከላከያ ሠራዊታችንን መደገፍ የግድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተደነገገ በኋላ በክልሉ አሸባሪውን  በመደገፍ ተጠርጥረው ተጨባጭ ማስረጃ ተገኝቶባቸው በቁጥጥር ስር የዋሉ እንዳሉ ጠቁመው፤ ተጠርጣዎቹን ለማስፈታት አንዳንድ አመራሮች ጭምር እየተሯሯጡ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

እነኚህ አመራሮች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የሀገር ሠላም በዋጋ አይተመንም፤  ሰርቶ ለመለወጥም ሆነ ወልዶ ለመሳም ሀገር ታስፈልገናለች ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ አልህድር አህመድ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከገባችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት  ሀገራዊና የዜግነታዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት መነሳሳታቸውን ነው  ያስታወቁት፡፡

ወይዘሮ ተዋበች ዘሌ በበኩላቸው፤  ህወሃት ጦርነት የማደርገው ከብልጽግና ጋር ነው  እያለ ንጹሃን ሰዎችን እና የቤት እንስሳትን ጭምር በመግደል ንብረት እየዘረፈ እና እያወደመ የሚፈጽመው እኩይ ድርጊት የጭካኔው ጥግ እንደሚያሳይ ይናገራሉ፡፡

ይህም ህዝብን በማጥፋት ኢትዮጵያ እንዳትቀጥል ማድረግ መሆኑን በግልጽ ያስረዳል ነው ያሉት የመንግስት ሠራተኛዋ፡፡

የመንግስት ሠራተኛው የአሸባሪው ቡድን ድብቅ የጥፋት እቅድ ከሌላው ማህበረሰብ በበለጠ የመረዳት እድል አለው የሚሉት ወይዘሮ ተዋበች፤ በህዝብ እና በሀገር ላይ እየደረሰ ያለውን  ጥፋት ለማስቆም የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ታዬ ቡሎ፤  አሁን በሃገራችን የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሃገር ከተደቀነብን የህልውና ፈተና ለመውጣት የግድ እና አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡

አዋጁን ለመተግበር የተደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሀገርን ለማዳን እየተካሄደ በሚገኘው የህልውና ዘመቻ እየጨመረ የመጣውን የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማስተጓጎል የአሸባሪው  ህወሃት ተላላኪዎች  በየአካባቢው የኢኮኖሚ አሻጥር እየፈጸሙ እንደሚገኙ  ጠቁመዋል፡፡

ከመንግስት ጋር በመቀናጀት ስርዓት ማስያዝ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የውይይት መድረኩን ከመሩት መካከል የክልሉ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ፤አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያውያንን አንድነት በመሸርሸር እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

አሁንም የጥፋት ቡድኑ በኢትዮጵያውያን እየተካሄደ የሚገኘው የህልውና ዘመቻ  ረጅም ጊዜ እንዲወስድ በማለም  የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የማስገባት ፍላጎት አለው ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ሠራተኞች በየትኛው ዘርፍ ቢሳተፉ ውጤታማ እንደሚሆኑ በመለየት ባለጉዳይን በአግባቡ ከማስተናገድ ጀምሮ እስከ ግንባር በመሰለፍ መስዋዕትነት መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የክልሉ የመንግስት ሠራተኞች ለህልውናው ዘመቻው ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ለሀገር ብሎም ለክልሉ ልማትና እድገት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት  የጋራ  መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም