ቀጥታ፡

አሸባሪው ሕወሃት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ራሳቸውን በማደራጀት በከፍተኛ ተጋድሎ አካባቢያቸውን ነጻ እያወጡ ነው

አዲስ አበባ፣  ህዳር 4/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሃት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ራሳቸውን በማደራጀት በከፋተኛ ተጋድሎ አካባቢያቸውን ነጻ እያወጡ መሆኑን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

ሕዝቡ ራሱን በማደራጀት በአሸባሪው ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መንግስት  ጥሪ አቅርቧል፡፡

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ እጅግ አስነዋሪ ግፍ እየፈጸመ ይገኛል፡፡

የሽብር ቡድኑ ሠላማዊ ዜጎችን ጨፍጭፏል፣ ንብረት ዘርፏል፣ መውሰድ የማይችለውን ደግሞ አውድሟል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ራሳቸውን በማደራጀት በሽብር ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሱበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ የጀግንነት ተጋድሎ አካባቢያቸውን ነጻ እያወጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዜጎች አካባቢያቸውንና አገራቸውን በመጠበቅ ረገድ እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ መንግስት ከፍተኛ አድናቆት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ከአፋር ሚሊሻና ልዩ ኃይል ጋር በመቀናጀት በወሰዱት እርምጃ አሻባሪ ቡድኑ በአፋር ክልልም ከፍተኛ ሠብዓዊ ኪሳራ ገጥሞታል ብለዋል።

በወረ ኢሉና አቅስታ በኩል ሰርጎ ለመግባት የሞከሩት የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ላይም የመከላከያ ሠራዊት ከአማራ ልዩ ሃይልና ሚኒሻ ጋር በመሆን እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን ላይ ባለፉት ስምንት ቀናት የተቀናጀ እርምጃ መወሰዱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በርካታ የቡድኑ አባላት ሲማረኩ ሌሎች ተደምስሰዋል ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና ሚኒሻ በጋራ በመሆን በሸኔ የሽብር ቡድን ላይ እየወሰዱት ባለው የተጠናከረ እርምጃ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ድጋፍ ከፍተኛ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ አሸባሪው ህወሓት የሸኔን የሽብር ቡድን በመጋለብ ፈጽሞ ወደ ስልጣን መምጣት እንደማይችል በተግባር ማሳየቱንም ነው ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያዊያን መንግስት ለህልውና ዘመቻው ላቀረበው ጥሪ የሰጡት ምላሽ የሚደነቅ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መከላከያውን በመቀላቀልም ሆነ በደጀንነት በማገዝ አገሩን እንደሚወድ በተግባር እያስመሰከረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ አኩሪ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ያለውን እውነት በትክክል እየተገነዘቡ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡

እነዚህ አካላት ሆነ ብለው የአሸባሪውን ህወሓት የጥፋት እንቅስቃሴ አይተው እንዳላዩ እያለፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ መንግስት ከሰሞኑን በኤርትራ ሠራዊት አመራሮች ላይ የጣለው ማዕቀብ አግባብ አለመሆኑን ኢትዮጵያ በጽኑ ታምናለች ነው ያሉት፡፡

የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ አሸባሪው ህወሓት ሆኖ ሳለ ማዕቀቡ ያነጣጠረው በተጠቂው ወገን ላይ መሆኑን በመግለጽ፤ ውሳኔው በቀጣናው ሠላም ከማስፈን ይልቅ ችግሩን እንደሚያባብስ ገልጸዋል፡፡

አሁንም ቢሆን በርካታ ዜጎች በአሸባሪ ቡድኑ ወረራ በከፍተኛ ሰቆቃ ላይ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህን ባለመገንዘብ የኢትዮጵያ መንግስት ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር እየተደራደረ ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።

በአሸባሪ ቡድኑ ወረራ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን መታደግ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም