አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት አልፏል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት አልፏል
ህዳር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አጋለጠ።
ኢሰመኮ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ በአሸባሪው ሕወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱም በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞኖች በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች የመልሶ መቋቋሚያ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመላክቷል።
የተፈጸሙ ጥሰቶች የጦር ወንጀል ስለመሆናቸው አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጾ፤ ከሰኔ 21 ቀን እስከ ነሃሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ በቡድኑ የተፈጸሙ የሰብዓዊ ምብት ጥሰቶችን ማጣራቱን ገልጿል።
“ምርመራው ባተኮረባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ እንዲሁም በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብሏል።
በተለይ የሕወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውንና ማቁሰላቸውን፣ ሰፊ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ሆን ብለው መፈፀማቸውን እንዳረጋገጠ ይፋ አድርጓል።
እንዲሁም የሕወሓት ኃይሎች ወደ ከተሞች ከባድ መሳሪያዎችን መተኮሳቸውን፤ በሲቪል ሰዎች መኖሪያ ቤቶች እና ቅጥር ግቢዎች ውስጥ ምሽግ በመቆፈር እና ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ ሲቪል ዜጎችን በአፀፋ ለሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች ጥቃት ማጋለጣቸውን በምርመራ እንደደረሰበት አመልክቷል።
በዚህም የበርካታ ሲቪል ሰዎች ሞት እና አካል ጉዳት እንዲከሰት እንዲሁም ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆናቸውን ሪፖርቱ አሳይቷል።
ኮሚሽኑ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተጨማሪ አካባቢዎች ቀጣይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ፣ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰፊ የሆነ የጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው ለተጎጂዎች አስፈላጊ የሥነልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ ድጋፍ መቅረቡን ጨምሮ በዚሁ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሰፊ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ “የተደረገው ምርመራ ሪፖርት ግኝቶች በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአፋጣኝ ማስቆም እንደሚገባ የሚያመላክት ነው” ብለዋል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።