ኮርፖሬሽኑ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የባቡር ማሰልጠኛ አካዳሚ ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የባቡር ማሰልጠኛ አካዳሚ ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ የባቡር ማሰልጠኛ አካዳሚ ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ። የአካዳሚው ግንባታ የሚከናወነው ኮርፖሬሽኑ ከቻይና መንግሥት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው። በቢሾፍቱ ከተማ በ151.7 ሔክታር መሬት የሚከናወነው የባቡር ማሰልጠኛ አካዳሚ የሰለጠነ የሰው ኃይል በአገር ውስጥ ለማፍራት የሚያስችልና ከጥገኝነት የሚያላቅቅ እንደሚሆን ተገልጿል። የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አዲስ የሚገነባው የባቡር አካዳሚ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞችን በተለያየ የዘርፉ ሙያ እያሰለጠነ የሚያወጣ ነው። ማሰልጠኛ አካዳሚው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከመካከለኛ ባለሙያ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ድረስ በብቃት የሚያቀርብ እንደሚሆን ጠቁመዋል። እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ የባቡር ማሰልጠኛ አካዳሚው ግንባታ በሁለት ምዕራፍ የሚከናወን ሲሆን በመጪው መስከረም ወር ተጀምሮ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል። ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅትም ግንባታውን ለማከናወን የዲዛይን፣ የግንባታ ቦታ የማዘጋጀትና ሌሎችንም ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት። አካዳሚው ከመካከለኛ ባለሙያ ጀምሮ የዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ዘርፉን ለማሳደግ የታለመ እንደሆነ ገልጸዋል። የአካዳሚው ወደ ስራ መግባት በአገሪቱ የባቡር ፕሮጀክቶች በራስ አቅም የሚከናወንባቸውን እድሎች የሚፈጥር እንደሆነ የተናገሩት አቶ ደረጀ የግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲጠናቀቅ በዓመት 1 ሺህ ሰልጣኞችን የሚቀበል መሆኑን ገልጸዋል። አካዳሚው የአስተዳደር ሕንፃ፣ የማሠልጠኛ ክፍሎች፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የመመገቢያ ክፍል፣ የተማሪዎች ማደሪያ፣ የመምህራን መኖሪያና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንፃዎች ይኖሩታል።