ቀጥታ፡

የስኳር ሕመም በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ነው

ህዳር 03 / 2014  (ኢዜአ የስኳር ሕመም በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ሲሆን በኢትዮጵያም ከስኳር ሁኔታ መዛባት ጋር የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር 12 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

የስኳር ሕመም ቀን ነገ በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ "የስኳር ሕመም ሕክምና እና እንክብካቤ ተደራሽነት አሁን ካልተተገበረ፤ መቼ?" በሚል መሪ ሃሳብ ለ31ኛ ጊዜ ይከበራል።

ቀኑን በማስመልከት የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ስኳር ሕመም ማኅበርና የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ከዓለም የስኳር ሕመም ተጠቂዎች 80 በመቶ የሚሆኑት በታዳጊ አገራት እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያም በሽታው የከፋ ጉዳት ከሚያስከትልባቸው አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ተጠቅሷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 563 ሚሊዮን ሰዎች የስኳር ሕመም ያለባቸው ሲሆኑ በኢትዮጵያ 12 ነጥብ 3 በመቶ ዜጎች የስኳር ሁኔታ መዛባት ችግር እንዳለባቸው ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ በመግለጫው ተነግሯል።

ከዚህም 3 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆኑት ከተረጋገጠ የስኳር ሕመም ጋር እንደሚኖሩና 9 ነጥብ 1 በመቶዎቹ በቅድመ ስኳር ሕመም ሁኔታ ውስጥ ያሉ መሆናቸውን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተገልጿል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሰለሞን እንዳሉት በኢትዮጵያ በተለያዩ የሕመም ምክንያቶች ወደ ሕክምና ተቋም ካልመጡ በቀር የስኳር ሕመም ምርመራ የማድረግ ልምድ ዝቅተኛ ነው።

በሽታው በዋናነት የሚመጣው እንቅስቃሴ ካለማድረግ፣ ስኳርና ስብ የበዛባቸውን ምግቦች በብዛት በመመገብና መሰል የጥንቃቄ ጉድለቶች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የስኳር ሕመም ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ ናቸው።

ማኅበሩ በስኳር ሕመም መከላከልና የሚያመጣቸውን ጠንቆች በተመለከተ ግንዛቤ የመስጠት፣ ለሕሙማን ኢንሱሊን የማድረስና የተለያዩ የምርመራ ግብዓቶች እንዲሟሉ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሕክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ትዕግስት መኮንን በበኩላቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በፍጥነት እየተስፋፉ በመሆኑ ትኩረት ያሻቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ማህበሩ በፖሊሲ የተደገፈና ቀጣይነት ያለው ስራ እንዲሰራ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ በፋብሪካ የሚመረቱ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ለማኅበረሰቡ ተደራሽ የሆነ የአመጋገብ ስርዓትን የያዘ የተቀናጀ መረጃ ሊኖር እንደሚገባና ለዚህም ሁሉም መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

የዓለም የስኳር ቀንን አስመልክቶ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተካሄዱ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በጤና ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ነፃ የስኳር መጠን ምርምራ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሂዷል።

በተጨማሪም ሕዳር 7 ቀን 2014 በጥቁር አንበሳ እና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ነፃ የስኳር መጠን ምርመራ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም