ቀጥታ፡

አሸባሪው ሕወሃት ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የአሜሪካን ድብቅ ፍላጎት የሚያስፈጽም ቡድን ነበር

ህዳር 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) "አሸባሪው ሕወሃት ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የአሜሪካን የምስራቅ አፍሪካ ድብቅ ፍላጎት የሚያስፈጽም ተላላኪ ቡድን ነበር" ሲሉ የኬንያው ፖለቲከኛ ፋራህ ማሊም መሃመድ ተናገሩ።

የቀድሞ የኬንያ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤና በጸረ ኢምፔሪያሊስት አቋማቸው የሚታወቁት ፋራህ ማሊም መሃመድ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከኦቢኤን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም አሸባሪው ሕወሃት አፍሪካዊ ማንነት እንዳይኖር የሚታገል ቡድን መሆኑን አንስተው፤ በተለይም የምስራቅ አፍሪካ  አንድነት እንዳይኖር አገራት እንዲበታተኑ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ቡድኑ በአገር ውስጥ የሚሰራውን እኩይ ሴራ በጎረቤት አገራትም ጭምር በመሥራት የቀጣናው አገራት እንዲከፋፈሉ ለማድረግ መስራቱን አስረድተዋል።

"ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ጎረቤቶቿን ኤርትራን፣ ሶማሊያን፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳንን በድሏል" ብለዋል።

"ቡድኑ በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ እንዲቆይ ያደረገው አሜሪካኖቹ ስለተቀበሉት ነው" ያሉት ፖለቲከኛው፤ ይህም አሜሪካኖቹ በመካከለኛው ምስራቅ ከተከተሉት አካሄድ ጋር እንደሚመሳሰል ጠቅሰዋል።

"አሜሪካኖቹ በምስራቅ አፍሪካ የሚፈልጉትን ማንኛውንም ነገር እውን ለማድረግ ህወሃትን እንደመሸጋገሪያ ድልድይ ተጠቅመውበታል" ብለዋል።

ቡድኑ በንጹሃን ኢትዮጵያዊያን ላይ ከባድ ግፍ ማድረሱን ጠቅሰው፤ በዘመነ ሥልጣኑ የብረት መዳፉ ያላረፈበትና ያልተንገላታ ሕዝብ ሊኖር እንደማይችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን በሚዲያዎቻቸው ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የሚቀሰቅሱበት መንገድ በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት የውክልና ጦርነት ማሳያ መሆኑን ያብራራሉ።

በተለይም በአዲስ አበባ ሰላም እንደሌለ አድርገው የሚያናፍሱት መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ከተማዋ ከአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የተሻለ ሰላም ያለባት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።   

ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን በማጠናከር አፍራሽ የውጭ ጣልቃ ገብነት በመከላከል የአገሪቱን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ጎን ለጎንም በሕዝብ ድምጽ ወደ ሥልጣን የመጣውን መንግሥት በመደገፍና አብሮ በመቆም ከውጭ የሚቃጣውን ጥቃት መከላከልና በጽናት መቆም እንደሚገባም መክረዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም