"የኢትዮጵያ ሠላም እስከሚረጋገጥ ቤት አለን ብለን የምንቀመጥበት ሞራል የለንም"

13

ህዳር 3/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በወራሪው የህወሓት የሽብር ቡድን የተከፈተባትን ጦርነት በድል እስከምታጠናቅቅና ሠላሟ እስከሚረጋገጥ አስፈላጊውን ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የኦሮሚያ ክልል ሴቶች ገለጹ።

በህወሓት የሽብር ቡድንና ግብረ አበሮቹ የተከፈተውን ጦርነት ለመመከት ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ እስከጫፍ በመነቃነቅ አለኝታነታቸውን አሳይተዋል።

በአዲስ አበባ ከሚገኙ የኦሮሚያ ቢሮዎች የተውጣጡ ሴቶችም የሚፈለገውን መስዋዕትነት በመክፈል ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን በሚል የንቅናቄ መርሃ-ግብር አካሂደዋል።  

በንቅናቄ መድረኩ ኢትዮጵያ በወራሪው የህወሓት የሽብር ቡድን የተከፈተባትን ጦርነት በድል እስከምታጠናቅቅና ሠላም እስከምትሆን የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሰርክአለም ሳኩሜ፤ የሽብር ቡድኖቹ ህወሓትና ሸኔ ከውጭ ሃይላት ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

ይህን አገር የማፍረስ ተግባር ለመመከት ሕዝቡ ከምንጊዜውም በላይ በጋራ መቆሙን ጠቅሰው ሴቶችም እስከ ወደ ግንባር ከመዝመት ጀምሮ የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ሴቶቹ "ሀገር ከሁሉም ነገር ትበልጣለች'' በማለት ሠላም ለማደፍረስ ገፍተው የመጡ ጠላቶችን ለመመከት የህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።  

አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ኢትዮጵያን ለማዳን ሴቶች በቁርጠኝነትና በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በመግለጽ ትግሉ አገር ነጻ እስክትወጣና ሠላሟ እስከሚረጋገጥ ይቀጥላል ብለዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮማንደር አሰበች ኃይለማሪያም በበኩላቸው የህልውና ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ በርካታ የኦሮሚያ ፖሊስ ሴት አባላት መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን ተናግረዋል።

መለዮ ለባሹ ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል በተለየ ለሀገር የማይከፍለው ዋጋ የለም ያሉት ምክትል ኮማንደር አሰበች "የኢትዮጵያ ሠላም እስከሚረጋገጥ ድረስ ቤት አለን ብለን የምንቀመጥበት ሞራል የለንም" ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ህጻናት ወታደሮቹን በየበረሃው እያሰለፈ በውሸት ፕሮፖጋንዳው ''አዲስ አበባ ልንደርስ ነው'' እያለ እየተጫወተባቸው ስለመሆኑም ምክትል ኮማንደሯ አንስተዋል።

የውጭ ሀይላትም የአፍራሽ ቡድኑን ተግባር እየደገፉና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን እያስገቡ በመሆኑ ይህንን እኩይ ተግባር ለመቀልበስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ ሆኗል ብለዋል።

የተቃጣባት ጦርነት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ኢትዮጵያ ወደ ሠላሟና ወደ ልማቷ የምትመለስበት ጊዜ ቅርብ ነው ብለዋል።

ባለቤታቸው በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛ መኮንን ሆነው በማገልግል ላይ እንደሚገኙ በማንሳት፣ እሳቸውም ለሀገር ሲሉ ልጆቻቸውን ትተው ወደ ግንባር ለመሄድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለአገራዊ ጥሪው ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ምላሽ ለመስጠት አቅም ያላቸው ወደ ግንባር በመዝመት፣ ለመከላከያ ሠራዊቱና ለጸጥታ አካላቱ ስንቅና ትጥቅ በማቅረብና የተፈናቀሉ ወገኖችን በማገዝ በቅንጅት እንደሚሰሩም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም