ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ ላሳየው ደጀንነት ምንም ዓይነት መስዋዕትነት ቢከፈልለት አይበዛበትም

ህዳር 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ ላሳየው ደጀንነት ምንም ዓይነት መስዋዕትነት ቢከፈልለት አይበዛበትም" ሲሉ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ተናገሩ።

የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራር ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ “ጦርነቱ ኢትዮጵያን እንደ አገር ሉዓላዊነቷን አስጠብቆ ማቆየት በሚፈልጉ አገር ወዳዶችና ሕልውናዋን ማጥፋት በሚሹ አሸባሪ ቡድኖች መካከል የሚካሄድ ፍልሚያ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ በሚደረገው ፍልሚያ የሠራዊቱ ጽናትና የሚፈጽመው ጀብዱ በታሪክ ማህደር በደማቅ ቀለም የሚፃፍ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለዚህም በአውደ ውጊያዎች የተሳተፋ ኢትዮጵያዊያንና የአሸባሪው ቡድን ምርኮኞች ጭምር ምስክር ናቸው ብለዋል።

ያም ሆኖ ኢትዮጵያዊያን በአውደ ውጊያ በመሳተፍ፣ የጠላትን መረጃ በመስጠት የፈጸሙት ደጀንነት በቃላት የሚገለጽ አይደለም ነው ያሉት።

ብርጋዴር ጄኔራሉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚኳትነውን አሸባሪው ህወሃት በገባበት ለመቅበር በሚደረገው ተጋድሎ "ሕዝቡ ላደረገልን ድጋፍ ማንኛውም መስዋዕትነት ቢከፈልለት ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም" ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያዊያን ላይ የከፈተው ጦርነት የህዝቡን አንድነት እንደ አለት ያጠነከረው መሆኑን ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚፋለመው የመከላከያ ሠራዊት የሽብር ቡድኑ ከገባበት እንዳይወጣ አድርጎ ይቀብረዋል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ቅንጣት ታህል ሊጠራጠር አይገባውም” ብለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም