ቀጥታ፡

የአፋር ሕዝብ የኢትዮጵያን ህልውና እና ዳር ድንበር ከመጠበቅ ዝንፍ ብሎ አያውቅም

ህዳር 12/2014 (ኢዜአ) የአፋር ሕዝብ የኢትዮጵያን ህልውና እና ዳር ድንበር ከመጠበቅ ዝንፍ ብሎ አያውቅም ሲሉ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ገለጹ።

መንግስት የተናጥል ተኩስ በማወጅ ይትግራይ ክልልን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ መፈዐሙ ይታወሳል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሚኖሩ ሰለማዊ ዜጎች ላይ ግፍ ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል፡፡

የአሸባሪ ቡድኑ የጭካኔ በትር ካረፈባቸው ህዝቦች መካከል የአፋር ህዝብ አንዱ ነው፡፡

ያነጋገርናቸው የሰመራ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እንደሚሉት፤ የአፋር ህዝብ በዘመናት ሁሉ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጡ ጠላቶችን በመመከት ይታወቃል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማሕበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የድህረ ምረቃ መርሃ-ግብር አስተባባሪ ሀቢብ መሓመድ 'የአፋር ሕዝብ መታወቂያው ድንበር ጠባቂነቱ ነው' ብለዋል።

የአፋር ሕዝብ በየዘመኑ የኢትዮጵያ ሉዓላዊንትና አንድነትን ለመጠበቅ በጽናት ሲታገል የቆየ ሕዝብ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

አሻባሪው የሕወሓት ቡድን የአፋርን ሕዝብ በውክልና ሲመራና ሲያሰቃይ መቆቱ ሳይበቃው አሁንም የጥፋትና ውድመት ሰለባ አድርጎታል ባይ ናቸው።

አሸባሪው ቡድን እስከመጨረሻው እስኪወገድ ድረስ ሕዝቡ እያደረገ ያለው ትግል ማጠናከር ምሁራንም  ከመንግስት ጋር የተናበበ ስራ መስራት አለባቸው ብለዋል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የጀመረውን ትግል አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ሀቢብ ያሳሰቡት።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ  ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሙክታር ጠይብ የአፋር ሕዝብ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ለጠላት ተንበርክኮ እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡

ህዝቡ የህወሓትን በደል የቀመሰና በቅርበት የሚያውቅ በመሆኑ እስከ መጨረሻው ይታገለዋል ብለዋል፡፡

የአፋር የእምነት አባት ሱልጣን አሊሚራህ " እንኳን እኛ ግመሎቻችንን የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቁታል" ያሉትን በማስታወስ፤ የአፋር ህዝን አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ህወሓት የአፋር ሕዝብ በመሰረተ ልማት እንዳያድግና ለውስብስብ ችግሮች እንዲጋለጥ እንደዳረገውም ነው የገለጹት፡፡

ሕዝቡ የአሸባሪውን ትክክለኛ ማንነት ስለሚያውቅ በተለመደው የጀብድ ታሪኩ አሸባሪውን እየተፋለመ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ገድል እየፈጸመ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብም አሁን እያደረገ ያለውን የጋራ ጠላትን በአንድነት የመመከት ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም