ቀጥታ፡

በለንደን ከተማ በአንድ ምሽት በተካሄደ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ከ11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተሰበሰበ

ህዳር 3/2014 (ኢዜአ) በእንግሊዝ መዲና ለንደን በአንድ ምሽት በተካሄደ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ከ11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተሰበሰበ፡፡

ድጋፉ የተደረገው ''የአንድ ሺህ እራት ለህዳሴ ግድብ'' በሚል በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲና በዩናንትድ ኪንግደምና አየርላንድ የህዳሴ ግድብ ድጋፍ ኔትወርክ በጋራ በመተባበር ባዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

በዩናትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ባስተላለፉት መልዕክት በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የኢኮኖሚ ጫና በጋራ መመከት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን የልማት እንቅስቃሴ ቀጣይነት ባለው መልኩ መደገፍ እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይበልጥ አንድነታቸውን በማጠናከር ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚሰራጩ ሀሰተኛ ዘገባዎችን መመከት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ለሀገራቸው እያበረከቱት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በዩናትድ ኪንግደምና አየርላንድ የህዳሴ ግድብ ድጋፍ ኔትወርክ ሊቀመንበር አቶ መንግሥቱ ጃብር በበኩላቸው የኢትዮጵያ እድገት፣ ሠላምና አንድነት የሚረጋገጠው በኢትዮጵያውያን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም "አንድነታችንን ማጠናከር ሀገራችንን ማዳን፤ መከፋፈል ደግሞ ሀገራችንን ለጠላት አሳልፎ መስጠት መሆኑን መገንዘብ ይገባል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠላቶች ፍላጎት የሚሳካው ኢትዮጵያውያን ከተከፋፈሉ ብቻ መሆኑንም አህጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በለንደን ዳያስፖራው ያሳየው ተነሳሽነት ኢትዮጵያን ለመደገፍ ለምናከናውናቸው የቀጣይ ስራዎች ወሳኝ ምዕራፍ የከፈቱ ናቸው ብለዋል፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም የዩናይትድ ኢትዮጵያ ሊቀመንበር ዶክተር ልዑልሰገድ አበበ፤ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን አጠናክረው ሀገራቸውን በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለው የኢኮኖሚ ጫናን ለመመከት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኮማቴው አባላት በቀጣይ ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም