አሸባሪው ህወሃትና ተላላኪዎቹ የደቀኑትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በአንድነት መነሳት ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃትና ተላላኪዎቹ የደቀኑትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በአንድነት መነሳት ያስፈልጋል
ጋምቤላ ኅዳር 3/2014(ኢዜአ)አሸባሪው ህወሃትና ተላላኪዎቹ በሀገር ላይ የደቀኑትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በአንድነት መነሳት እንደሚያስፈልግ የጋምቤላ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
የሀገር ሽማግሌዎቹና ታዋቂ ግለሰቦቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ዜጎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አመልክተዋል።
የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ኃይለማሪያም ተክለማሪያም ፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለ27 ዓመታት በክልሉ ብሄር ተኮር ጭፍጨፋ ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ደግሞ ቡድኑ የኢትዮጵያ ህልውና ለማጥፋት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ማንም የዳር ተመልካች መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል።
በተለይ የክልሉ ሕዝብ ቡድኑና ተላላኪዎቹ ሀገር ለማፍረስ የከፈቱትን ጦርነት ለመቀልበስ ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ መስዋትነት ለመክፈል መዘጋጀት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
ሀገርን ከጥፋት ማዳን ለመከላከያ ሠራዊት ብቻ የማይተው በመሆኑ ዜጎች ባላቸው መሣሪያ ሕዝባዊ ጦርነቱን እንዲቀላቀሉ ሰብሳቢው መልዕክት አሰተላልፈዋል።
ከሽግግር መንግስት ጀምሮ በነበራቸው የአመራርነት ቆይታ የአሸባሪው ቡድን ተንኮልና እኩይ ሴራ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ በማስታወስ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ ሌላው የሀገር ሽማግሌ አቶ ቦል ኬት ናቸው።
ቡድኑ እያካሄደው ያለው ወረራ ባለፉት ዓመታት ሲፈጽማቸው የነበሩትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችና ዘረፋ ለመድገም በማሰብ እንደሆነም አስረድተዋል።
በሀገር ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ ዜጎች ወደ ግንባር በመዝመት ቡድኑን ግብዓተ መሬት ለመፈጸም መነሳት አለብን ብለዋል።
የቀድሞው የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ጋህነን) ታጋይ አቶ ፒተር አማን በበኩላቸው ''ህወሓት በተንኮልና በሴራ ተወልዶ ያደገ 'የጭቃ ውስጥ እሾህ ነው' ሲሉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን አጠናክሮ በትብብር ከሰራ አሸባሪው ቡድን የደቀነውን አደጋ ለማለፍ የሚያዳግት ነገር አይኖርም ብለዋል።
በተለይም ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊት ያለውን ደጀንነት በተግባር በማሳየትና በመዝመት የሀገሩን ህልውና ለማረጋገጥ እንዲረባረብ ጠይቀዋል።
የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ባለፉት ሁለት ቀናት በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ መምከራቸውን ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል።