ቀጥታ፡

አድዋ የጀመርነውን ጦርነት ዋሽንግተን ዲሲ እንደምድመው!

የዚህ ጽሁፍ ባለቤት መልካሙ ዘርይሁን ኣስራት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ፋኩልቲ በፕሬስ ጋዜጠኝነት በዲፕሎማ እና በሬዲዮ ጋዜጠኝነት በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ፤ 'ንጉስ አርማህ' እና 'ህንደኬ' የተሰኙ ታላላቅ ታሪካዊ ተውኔቶችን ጽፎ ለእይታ ያበቃ እንዲሁም 'የኛ እድር' የተሰኘ ሳታየር ኮሜዲ ደርሶ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች፣ በውጭ አገር በለንደንና ዋሽንግተን ከተሞች የታየለት ታላቅ የኪነጥበብ ሰው ነው።

ኢትዮጵያ ለመላው ዓለም ግልጽ በሆነ መንገድ የነጮችን ተስፋፊና ግፈኛ የኮሎኒያሊዝም ስርአትን አድዋ ላይ መግታት ችላለች፡፡ ይሄ ለመላው የአፍሪካውያን፣ ካሪቢያን፣ የአሜሪካን ጥቁሮችና ሌሎች በዓለም ላይ እንደጨው ተበትነው ለጭቆናና ባርነት ተዳርገው ለነበሩ ህዝቦች ብርሀንን የፈነጠቀ ተስፋን የጫረ ነጻነትንና ነጻ መሆንን ያስተማረ ታላቅ ታሪክ ጽፎ አልፏል፡፡

ለኛ ለኢትዮጵያውያን ግን (we won the battle not the war) እንደሚሉት አድዋ የመከራችን መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ ሊሆን አልቻለም፡፡

ያሸነፍነው አንዲቷን ውግያ እንጂ መላ የነጭ የበላይነት ስርአትን አልነበረም፡፡ ያንን መነቅነቅ እንጂ መጣል አልቻልንም፡፡ ጭራሽ ይሄ ስርአት ራሱን ወደ ተሻለ ማንነት ቀይሮ ኮሎኒያሊዝምን ‹‹ያረጀ ፈረስ›› በሚል የዳቦ ስም አውጥቶለት፣ አጣጥሎ አዲስ ያለውን የአለም ስርአት ዘረጋ፡፡ ይህም አዲስ የአለም ህብረት ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽን›› ከአድዋ የቀጠለውን ጦርነት በተቋቋመ ማግስት በኢትዮጵያ ላይ ጀመረ፡፡ ሁሉም ነጭ መንግስታት ጦርነቱን ደገፉት፡፡

በመርዝ ጋዝና በታንክ፣ በአካፋና በዶማ ኢትዮጵያውያንንና ኢትዮጵያን ጨፈጨፉ፤ ቂሙን ቋጥሮ የመጣው የነጭ ወራሪ ሀይል ኢትዮጵያዊነትን ለማዋረድ የቻለውን ሁሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን አደረገ፡፡ በገዛ ትግላችንና እምቢ ባይነታችን የነጭ ወራሪ ሀይልን ከሀገር ቢወጣም፣ አሁንም ከአድዋ ሽንፈታቸው የቀጠለ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማዋረድ በርካታ ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሀይማኖታዊ አፍራሽ ተልእኮዎችን በኢትዮጵያ ላይ እና በመላ ጥቁር ህዝቦች ላይ ቀጠለ፡፡

የስልሳዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የነጮቹና የግብጻውያን ፖለቲከኞች ሰርጎ ገብነት ገሀድ በሆነ መልኩ መታየቱ ታሪክ መዝግቦት የሚገኝ ሀቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለምእራቡ ዓለም አጎብዳጅ የሆነ መንግስት እስካላቋቋመች ድረስ የነጮች የበላይነት (neo-colonialism) አሁንም የአድዋውን ሽንፈት ለማካካስ ከቀደሙ የነጭ ስርአቶች በወረሰው ግብ መሰረት የሚደረገው ትንቅንቅ መቀጠሉን በሚገባ የተረዳንበት ግዜ ላይ ደርሰናል፡፡

ከአድዋ ምን አገኘን? ምንስ አጣን?

እኒህን ጥያቄዎች እኛም ሆንን መሪዎቻችን በሚገባ መጠየቅ የሚገባን ግዜ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡

ከአድዋ ያገኘነው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚገባ በደም ባጥንቱ የሚረዳው ነፃ መሆንንና ነፃነትን፣ በራሳችንን ጉዳይ ራሳችን መወሰንን አግኝተናል፡፡ ዓለም ፊት ራሳችንን በኩራት ኢትዮጵያዊ ብለን ለመጥራት ችለናል፡፡ ከራሳችን አልፈን አፍሪካውያንና ጥቁር አሜሪካውያን የሚኮሩበት ታሪክ ጽፈን አሁንም ከትውልድ ትውልድ ይተረካል፡፡ ዛሬም በኢትዮጵያዊነታችን በነፃነታችን የመጣን ጠላት ፊት ለፊት ለመጋፈጥ አናፈገፍግም፡፡

ከአድዋስ ምን አጣን?

በነጭ የበላይነት በምትመራው ዓለም፣ የቅድሚያ ቅድሚያ ለእድገት መሰረት የሆነውን ሰላማችንን መቼም ቢሆን እንዳናገኘው በምክንያት ጦር ይከፈትብናል፡፡ ለውጭ ጣልቃ ገብነት ተጋላጭ መንግስት እንዲኖረን ቀን ከሌት የፖለቲካ ደባ ይጎነጎንብናል፡፡ ከልጅ እያሱ ጀምሮ ለምእራቡ ዓለም ያላጎበደደ መሪ ተጋላጭ ሆኖ ከውስጥም ከውጭም ጠላት ይገዛበታል፡፡ የኦጋዴን ጦርነት፣ የሻእቢያና ወያኔ የ30 ዓመቱ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እንዲሁም አሁን በመካሄድ ላይ ያለው አሸባሪው ህወሓት የቆሰቆሰው ጦርነት ዋና ዋና ከሚባሉት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ለዚህ ሁሉ የፖለቲካ ውጥንቅጥ የመጀመሪያ ተወቃሾቹ እኛው ራሳችን ስንሆን፣ ስህተቱም አድዋን የኛ የግላችን ታሪክ አድርገን ማስቀረታችን ብቻ ሳይሆን፤ ይኸው ታሪክ የመላ ጥቁር ህዝቦች ታሪክ እንደሆነ ለማሳየት የተደረገ ከራሳችን ከኢትዮጵያውያን የወጣ ምንም አይነት የትግል እንቅስቃሴ አለመኖሩ ድሉን ምሉዕ እንዳይሆን አስችሎታል፡፡

ጥቁር ህዝቦች የአድዋን ድል የሚኮሩበትን ያህል የባርነት፣ የኮሎኒያሊዝም አስከፊ ታሪካቸውን እንባና ጥልቅ ቁስል እንዲያብሱበት አላደረግንም፡፡ ገድሉንም፣ ድሉንም ነጠቅናቸዋል፣ ከአድዋ ድል ባይተዋር እንዲሆኑ አደረግናቸዋል፡፡ የነማርክስ ጋርቤይን ትግል ጎትተን ወደ መሀል ከማምጣት ይልቅ እንደማናቸውም ሰው ታዛቢ ከመሆን አላለፍንም፡፡ ጭራሽ ድሉን የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ አደረግነው፡፡ ያኔም አሁንም ጥቁሩን አፍሪካዊ ሆነ አሜሪካዊ እንቁልልጭ የማለት ያክል በዚህን ታላቅ የአያቶቻችን ገድል ላይ አላገጥን፡፡

የአድዋን አህጉራዊና አለማቀፋዊ ድባቡን ከነአካቴው አጠፋነው፡፡ አሁንም ድረስ እኛ ብቻ ከዓለም ተከልለን የምናከብረው፣ እኛ ብቻ የምንኮራበት፣ የምንሸልልበት፣ የምንፎክርበት ሆኖ እንዲቀር አድርገናል፡፡

ጦርነቱን ባሸነፍንበት ማግስት ከዚያም በኋላ በዓለም የተበታትነው የባርነት መራር ፅዋ ይጎነጩ የነበሩ ጥቁር ህዝቦች አጋርነታችንን አለመግለጽ፣ ለዚያም የሚበጅ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አለማድረጋችን ለምእራቡ ዓለም ፕሮፓጋንዳ ተመቻቸን፡፡ ከአለማቀፍ የጥቁር ህዝቦች ትግል ተነጠልን፡፡

ወደ ኋላ አፄ ሀይለስላሴ የአፍሪካ አንድነትን ለማቋቋም ትልቅ ጥረት ቢያደርጉም ስራቸው የረፈደ በመሆኑ አሁንም ድረስ የተባበረ የአፍሪካ አገርን ማየት አልቻልንም፡፡

በአንጻሩ አውሮጳውያን የነጭ የበላይነትን ስርአት ለአሜሪካን አሳልፈው በመስጠት አሁንም ድረስ ትሩፋቱን እያጣጣሙ ይገኛሉ፡፡ በጥቁር ህዝብ ደምና ላብ ትርፋቸውን በመቁጠር ላይ ናቸው፣ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን፣ ዛሬም ከባርነት አስተሳሰብ አልወጡም ‹ቼ› ሲባል እንደ ሚፈረጥጥ ፈረስ በምእራቡ አለም መሪዎች እንደደነበሩ አሉ፡፡ ሰሞኑን እንኳ የዛምቢያው ፕሬዚዳንት የዲፕሎማቲክ ሰራተኞቻቸውን ከአዲስ አበባ ሲያስወጡ ቀድመው እንዲሰሟቸውና አበጁ እንዲባሉ የፈለጉት ከህዝባቸው ሳይሆን ከነጮቹ ነበር፡፡

አሁን ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም የታሪክ ዘውግ ውስጥ ታላቅ ሀውልት ለማቆም የታጨንበት ግዜ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ አስቀድመን እጁን የቆረጥነው የነጭ የበላይነት ትግልን የመምራት ታሪካዊ፣ አፍሪካዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ሀላፊነት አለብን፤ የአድዋን ከፊል ድል ሳይሆን ሙሉ ጦርነት ከመቶ ምናምን አመት በኋላ የምናሸንፍበት እድል በእጃችን ገብቷል፡፡ አያቶቻችን የጀመሩትን የነፃነት ችቦ በመላ ጥቁር ዓለም ላይ ያለስስት ያለ መስገብገብ ከፊት ቆመን ከአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በመጣመር የምናንቦገቡግብት ሰዓት ላይ ነን፡፡

በስመ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት የተለወሱትን የነጮች የበላይነት መንጸባረቂያ  የሆኑትን አለማቀፍ ተቋማት በቃ! (no more) የምንልበት ወርቃማ ሰዓት ይቺ ሰከንድ መሆን ይገባታል፡፡

በመላ አፍሪካ የሚገኙ ዲፕሎማቶቻችን፣ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ወዳጆች በተለያዩ መንገዶች እንዲያውቁት፣ እንዲረዱትና ከጎናችን እንዲቆሙ በማስረዳት፣ አሁን የምናደርገው ጦርነት የአድዋ ቀጣይ እንጂ የተለየ አለመሆኑን ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ በአሜሪካን የሚኖሩ መላ ጥቁር ህዝቦች የዚህ ትግል ዓላማ በማስረዳት በቨርጂንያ የአካባቢ ምርጫ ወቅት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ያደረጉት ቁንጽል የምርጫ ተጽእኖ በመላ አሜሪካ በማፋፋም በመላ አሜሪካን የሚቀጣጠል ሰደድ በማድረግ፣ ትግሉን አለማቀፋዊና የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል ማድረግ ይገባል፡፡

ለዚህ መስዋእትነት እኛ ኢትዮጵያውያን ከፊት ቀድመን አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንዲከተሉ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ያለ መስዋእትነት የሚገኝ ምንም ድል እንደሌለ ማሳየት አሁንም የኛ እውነተኛ ተግባር መሆን ይገባዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ዓለማቀፍ ትንቅንቅ ውስጥ መሽኮርመሙን ትቶ የጥቁር ህዝቦች የተባበረ ክንድን እርዳታ በግልጽ በመጠየቅ፣ በአድዋ የተሰራውን ስህተት በማያዳግም መልኩ እንደማይደገም ቃል በመግባት አለማቀፍ ትግሉን በመጫር ማቀጣጠል ይገባዋል፡፡

ይህን ማድረግ ከተቻለ፣ ከመቶ አመታት በፊት የተጀመረውን ለከፍተኛ ረሀብ፣ ድህነት መሀይምነትና የእርስ በእርስ ጦርነት የዳረገንን የአድዋ ድል ማግስት ወረርሽኝ፣ በአለማቀፋዊ የጥቁር ህዝቦች ትግል ዳር የምናደርስበትና ከምር በራሳችን የምንኮራ ጥቁር ህዝቦች ብቻ አይደለንም፤ ይልቁንም መላ ጥቁር ህዝቦች ዳግም ኢትዮጵያዊያን የሚሆኑበት፣ ለአለም ስጋት ሳንሆን የስልጣኔ ቀንዲል ለኳሾች መሆናችንን ለነጩ ዓለም የምናበስርበት፣ የተዳፈነውን የጥቁር ህዝቦች ስልጣኔ ከመሬት ስር ሳይሆን ከጥቁር ህዝቦች አእምሮ ፈልቅቀን የምናወጣበትን ብርቅ ዘመን እናመጣለን፡፡

እናም የኢትዮጵያን እውነት በማስገንዘብ ያለውን መልካም ግንኙንት ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ስለ አገሪቷ ያለውን አረዳድ በማስተካከልና ሰላማዊ በማድርግ ዲፕሎማሲያዊ ድሉን ዋሺንግተን ዲሲ ላይ እንደምድመው ስል ጥሪዬን አቀርባለሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም