ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና መጠበቅ እንደ አድዋ የድል ዘመን በፍፁም አርበኝነት ስሜት ከዳር እስከዳር እየተንቀሳቀሱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና መጠበቅ እንደ አድዋ የድል ዘመን በፍፁም አርበኝነት ስሜት ከዳር እስከዳር እየተንቀሳቀሱ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና መጠበቅ እንደ አድዋ የድል ዘመን በፍፁም አርበኝነት ስሜት ከዳር እስከዳር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተገለፀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀ 'አዲስ ወግ' የውይይት መድረክ “የሕልውና ጥሪ እና ሀገርን የማዳን ርብርብ” በሚል ርዕስ ተካሄዷል፡፡
በመድረኩ የውይይት መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ናቸው።
አሸባሪው ህወሃት "ኢትዮጵያን እኔ ካልገዛሁ አፈራርሻት በፍርስራሿ ላይ እኖራለሁ" በማለት ጦርነት መክፈቱን አንስተው፤ ዓላማውን ለማሳካት ደግሞ ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጋር በህብረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ ቁሳዊና ሰነ-ልቦናዊ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸው፤ ለጦርነት ከመሳሪያ፣ ከሰው ኃይል ዝግጅቱ በተጨማሪ የትግራይ ህዝብን ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ለመነጠል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሰላምና ደህንነት በሚል የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያደርግም፤ የሽብር ቡድኑ በአፋርና በአማራ ክልሎች ወረራ በመፈጸም አስከፊ ግፍ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አሸባሪ ቡድኑ እያፈጸመ ላለው ግፍና ሰብዓዊ ጥሰት የሰጠው ምላሽ እጅግ የሚያሳዝን መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊያን የገጠማቸውን ፈተና እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለጋራ ህልውናቸው እንደ አድዋ ድል ዘመን በፍፁም አርበኝነት ስሜት ከዳር እስከዳር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያዊያን የጠላት ፍላጎትና ሐሳብ እንደማይሳካና ኢትዮጵያም የማትደፈር አገር መሆኗን ለዓለም በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።
የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር እንደሻው ጣሰው፤ አንዳንድ የምእራባውያን ሀገራት መገናኛ ብዙሃን ተቋማት በሀሰተኛ መረጃ የኢትዮጵያን ምስል የማጥፋት ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ኢትዮጵያውያን በአንድነት እያከናወኑ ያሉት የህልውና ዘመቻ እንዳይሳካ ለማድረግ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ሀሰተኛ መረጃዎችን ከማጋራት መቆጠብና በሀሰተኛ መረጃ የተከፈተብንን የስነ-ልቦና ጦርነት በሚገባ መመከት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
በውይይቱ ላይ አስተያየት የሰጡት የፖሊሲ ጥናት ኢንስትቲዩት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አሸባሪው ህወሓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የጭካኔ ግፍና ዘረፋ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ በአረጀ ሃሳብ የሚመራ መሆኑን ገልጸው፤ በወረራ በያዛቸው ክልሎች ላይ እየፈጸመ ያለው ጥቃት ለህዝቦች ያለውን ጥላቻ ያሳያል ብለዋል።
እየተደረገብን ያለው ዘመቻ እንደ ሀገር እንዳንቀጥል የማድረግ ሴራ ነው ያሉት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቤኒ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ ናቸው፡፡
በመሆኑም የህልውና ዘመቻው ዳግማዊ የአድዋ ዘመቻ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡