ቀጥታ፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት ካላት በህዝብ ድምጽ ወደ ስልጣን የመጣውን መንግስት መደገፍ አለባት

ህዳር 2/2014 (ኢዜአ) አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ፍላጎት ካላት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራውን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት መደገፍ አለባት ስትል ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ ተናገረች።

የሲ ቢ ኤስ ጋዜጠኛዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊቷ ሔርሜላ አረጋዊ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ጋዜጠኛ ሄርሜላ፤ የአሜሪካ መንግስት በምርጫ ሥልጣን የያዘ መንግሥትን የሕወሓት የሽብር ኃይል ጋር እኩል የመመልከት አዝማሚያ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣ መፍጠሩን ትገልጻለች።

በተለይም ደግሞ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በኃይል ለማውረድ በዋሺንግተን ዲሲ ተመሰረተ እየተባለ የሚባለው የፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት የአሜሪካን ወገንተኝነት ማሳያ መሆኑን አንስታለች።

ይህም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያ ወዳጆች አሜሪካ ለሕወሓት እንደ ወገነች እንደሚያምኑ ማድረጉን ገልጻ፤ አሜሪካ እየተከተለች ያለችው አካሄድ ትክክል ባለመሆኑ ሊስተካከል ይገባል ብላለች።

በርካታ ኢትዮጵያዊያን ይህ የአሜሪካ አቋም እንዲቀየር ጥረት አያደረጉ መሆኑንም ነው የተናገረችው፡፡

አሜሪካ አሸባሪው ሕወሃትን የወገነ አካሄድ እንድትከተል ያደረጋት የቡድኑ የቀድሞ ባለስልጣናት በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ ካሉ አንዳንድ ሰዎች ጋር ባላቸው የጥቅም ፍላጎት ሊሆን እንደሚችልም ጠቁማለች።

ከዚህ አኳያ ለአሜሪካና ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም የሚበጀው አሜሪካ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራውን ሕጋዊ መንግሥት ስትደግፍ መሆኑን አስረድታለች።

መንግሥት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ለሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የኢትዮጵያን አቋም በግልጽ ለማሳወቅ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ተናግራለች።

በተለይም አዲስ የተቋቋመው የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ተቋም የተግባቦት ሥራን ይበልጥ በማጠናከር በቀጣይ የተሻሉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጻለች።

ዜጎችም ለሐሰተኛ መረጃዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ የሚደርሷቸውን መረጃዎች ከትክክለኛ ምንጭ መውሰዳቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ጋዜጠኛ ሔርሜላ አሳስባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም