የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት በሶስት ሳምንት ውስጥ 100 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብስብ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት በሶስት ሳምንት ውስጥ 100 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብስብ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 2/2014/ኢዜአ/ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት በሶስት ሳምንት ውስጥ 100 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብስብ በማቀድ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ህዝብ ፕሬዝዳንት አቶ ጋሻው ሽባባው ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ተወካዮች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት፣ ጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ነው ስምምነቱ የተፈረመው።
በስምምነቱ መሰረት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለ21 ቀናት ደም የመሰብሰብ መረሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል፡፡
የደም ልገሳው ለአገር ሉዓላዊነት እየተዋደቀ ላለው የመከላከያ ስራዊትና ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚውል መሆኑን አቶ ጋሻው ገልጸዋል።
ጥምረቱ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደም በመሰብሰብ፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ፣ መልሶ የማቋቋም ስራ እየሰራ ይገኛልም ብለዋል።
በህግ ማስከበር ዘመቻው ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች በመጠገን ወደ ስራ እንዲገቡ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በጥምረቱ ከ300 በላይ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ከህዝብና ከመንግስት ጎን ሆነው እየደገፉ መሆኑን አብራርተዋል።
በስምምነቱ ወቅት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታየ ደንዳአ፡ መተኪያ የሌለውን ህይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረግና ማክበር የሁሉም ግዴታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፡ ደም መስጠት ሰብዓዊነት በመሆኑ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ደራሽ ልንሆን ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የከፈቱት አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ብቻ አይደሉም ያሉት ኮሎኔል ጌትነት ከውስጥና ከውጭ የመጣብንን ጠላት በጋራ መመከት አለብን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል ባንቴ፡ የተደረገው ስምምነት ከምንጊዜውም በላይ ደም በሚያስፈልግበት ወቅት ነው ብለዋል።
ዜጎች ደም መለገስን እንደባህል በማድረግ የሰዎችን ህይወት እንዲያተርፉ ጥሪ አቅርበዋል።