ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ህዳር 2/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሔራን ገርባ፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

በተለይም አሸባሪው ህውሓት በከፈተው ጦርነት በርካታ ንጹሃን የተለያየ ጉዳት የገጠማቸው ሲሆን ብዙዎች ደግሞ ለአስከፊ ችግር ተጋልጠዋል ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ መረዳዳትና መደጋገፍ ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሪት ሔራን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

''ያጋጠመው ችግር የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ በመሆኑ አንድነታችንን የምናሳየው በዚሁ በመደጋገፍ ተግባር ሊሆን ይገባል''ብለዋል።

የባለስልጣኑ ሰራተኞች ያዋጡትን ከ700 ሺህ ብር በላይ ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የስትራቴጂክ ሎጂስቲክ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አይድሩስ ሃሰን፤ ድጋፉ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የሚገኙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ በአፋር ክልል 200 ሺህ ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 400 ሺህ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቅሰው በሌሎች አካባቢዎችም እንዲሁ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ለነዚሁ ዜጎች ከእለት ደራሽ የምግብ አይነት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ የግድ መሆኑን ጠቅሰው የባለስልጣኑ ሰራተኞች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ መንግስት 70 በመቶውን እየሸፈነ ይገኛል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም