ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በእኛ ላይ የፈጸመው ግፍ በአሁኑ ትውልድ እንዳይደገም ለመታገል ቆርጠን ተነስተናል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 02/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በእኛ ላይ የፈጸመው ግፍ በአሁኑ ትውልድ እንዳይደገም ለመታገል ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ተናገሩ፡፡

በህልውና ዘመቻው በመሳተፍ ለአገራቸው ሉዓላዊነት የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው  የተናገሩት፡፡

አሸባሪው ህወሓት የሀገር ምልክት የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት አባላት በፓርቲና ግለሰብ ስም በመለጠፍ ክብራቸውን ዝቅ ለማድረግ ሲጥር ይታያል፡፡

የአሸባሪ ቡድኑ ተግባር ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የቀድሞ ሰራዊት አባላት ላይ  የተለያዩ ስሞችን በመለጠፍ ግፍ ሲፈጽምባቸው ቆይቷል፡፡

በቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የከባድ መሳሪያ ምድብተኛ የነበረው ወታደር መልካሙ መንግስቴ አሸባሪ ቡድኑ በስልጣን ላይ እያለ እያራመደው በነበረው ስርዓት ውስጥ ሊስተካከሉ የሚገባቸውን ችግሮች በመናገሬ ብቻ ለእስርና እንግልት ተዳርጌያለሁ ሲል ይገልጻል፡፡

ይህ አልበቃ ብሏቸው የመከላከያ ሰራዊቱን ዳግም ተቀላቅዬ ሀገሬን ሳገለግል ከነበርኩበት የውትድርና ሙያ እንድቀነስ አድርገውኛል ነው ያለው።

በዚህም ልጆቹንና ቤተሰቡን የሚያኖርበት ገቢ በማጣት ለከፋ ችግር ተዳርጎ መቆየቱን ነው የሚናገረው፡፡

በመሆኑም በእኔ ላይ የደረሰው ግፍ በልጆቼ እንዳይደርስ ዛሬ አገራዊ ጥሪውን በመቀበል አሸባሪ ቡድኑን ለመዋጋት ዝግጁ ሆኛለሁ ብሏል።

የአሸባሪ ቡድኑ ግፍ ዳግም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር እንዳይደገም አድርጎ መደምሰስ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑንም ተናግሯል፡፡

ወታደር ኤልሳ ዶሎና ወታደር አለማየሁ ኢተፋ የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ከዚህ ቀደም  ‘’የደርግ ወታደር’’ አሁን ደግሞ ‘’የአብይ ወታደር’' በማለት የኢትዮጵያ ህልውና መሰረት የሆነውን ሰራዊት ለማዳከም እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት "እኔ ሞቼ አገር ትቀጥል" በሚል ለአገራቸው ህልውና ህይወታቸውን ሳይሰስቱ በሰጡት የቀድሞ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመውን ግፍ ሁሉም ሊገነዘበው እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የቀድሞ ሰራዊት አባላት የሆኑት ወታደር ብርሃኑ አኬሾና አቶ ኤልሳ ዶሎ ናቸው፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ጠብቀው ሀገርን ከውጭና ውስጥ ጠላቶች መከላከል አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ወታደር መንበረ ቀፀላ በበኩላቸው በህልውና ዘመቻው የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት  ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም