አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጩት ዘገባ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርተው ነው - ኢዜአ አማርኛ
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጩት ዘገባ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርተው ነው
ህዳር 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጩት መረጃ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ባለገናዘበ መልኩ መሆኑን በእንግሊዝ የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሰሐ አዱኛ ገለጹ።
አምባሳደር ፍስሃ ፋይናንሻል ታይምስ ያወጣው የተሳሳተ መረጃ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የዘነጋ መሆኑን አስረድተዋል።
አምባሳደሩ እንዳመለከቱት በጋዜጣው ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ.ም ርዕስ አንቀጽ ላይ የተስተናገደው ሃሳብ የተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው።
በዕለቱ እትም “ኢትዮጵያ አዲሲቷ ዩጎዝላቪያ የመሆን ስጋት አጥልቶባታል” በሚል ርዕሰ አንቀጹ ያስነበበው ጽሁፍ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ ያላገናዘበና ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን ገልጸዋል።
ጉዳዩን አስመልክተው ለጋዜጣው በሰጡት ምላሽና በጋዜጣው በተስተናገደው የአምባሳደሩ ጽሁፍ ፋይናንሻል ታምስ ያለአግባብ የኢትዮጵያን መንግሥት መውቀሱ ተገቢነት የሌለው ነው ሲሉ ኮንነውታል።
ጋዜጣው ያልተገባ መረጃ ለንባብ ማብቃቱ ፍጹም የተሳሳተ ከመሆኑ ባለፈ ግጭቱን አስመልክቶ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሚኖረው ግንዛቤ በጣም አደገኛ መሆኑንም አስምረውበታል።
እንደ አምባሳደሩ ማብራሪያ በጋዜጣው የሰፈሩ ሃሳቦች በብዙ መልኩ በተሳሳተ መንገድ መገለፃቸው አግባብነት የለውም ብለዋል።
በተለይ የግጭቱን አጀማመር አስመልክቶ ጋዜጣው ያነሳው ሃሳብ ሆን ተብሎ የተደረገ ስህተት በመሆኑ ሊታረም ይገባል ነው ያሉት።
ጦርነቱን በመጀመር ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ የሚወስደው አሸባሪው ህወሓት ብቻ እንደሆነም አምባሳደር ፍሰሃ ግልጽ አድርገዋል።
ባለፈው ዓመት ኅዳር መጨረሻ የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ቲቦር ናዥ “ህወሓት ያጣውን ሥልጣኑን ለመመለስ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍቷል” ሲሉ መናገራቸው ይህንኑ ሃቅ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በህዝብ ይሁንታ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከተመረጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ገንቢ ትብብር በመፍጠር ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚገባውም አምባሳደር ፍሰሃ አመለክተዋል።