ቀጥታ፡

መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ሰርቷል፤ እየሰራም ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 02/2014 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ከማድረግ ጀምሮ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ሰርቷል፤ እየሰራም ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል- አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አካላት ጋር ጠቃሚ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት የአሜሪካ አፍሪካ ጉዳዮች ልዩ መልእክተኛ ጀፍሪ ፊልትማን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮችና የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፍቲ ጋር መወያየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው የአማራና አፋር ክልሎች ዘረፋና ኢ-ሰብዓዊ ግፎችን እና የሰብዓዊ አቅርቦት ማስተጓጎል በተመለከተ ለባለሥልጣናቱ እንደተገለጸላቸው አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን ከአጎዋ ማገዱ አግባብ አለመሆኑንና ይልቁኑም የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያበላሽ መሆኑን ማንሳታቸውን ገልጸዋል፡፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላት ተዕጽኖ ምክንያቱን እንደማያውቁ ገልጸው፤ እየሻከረ የመጣው የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት እንዲሻሻል በሁለቱም አገሮች በኩል ፍላጎት መኖሩን መግለጻቸውን አንስተዋል።

የአፍሪካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ የሰላም እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና የተለያዩ ወገኖችን ማነጋገራቸውንም ጠቁመዋል።

መንግስት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በርካታ ጊዜ የሰላም ጥረቶችን ማከናወኑንም አውስተዋል።

ከሰሜን ዕዝ ጥቃት በኋላ መንግስት ተገዶ ከገባበት ጦርነት በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎና ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከሰሞኑም ለኢትዮጵያ ሰላም መፍትሔ በመሻት ወደ ኢትዮጵያ ለመጡት ለቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ "ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" የሚለውን መርህ ኢትዮጵያ የምትደግፈው ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሁሌም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥታ የምትሰራ ሀገር መሆኗን ገልፀው፤ ኢትዮጵያ በአስገዳጅነት የገባችበት ጦርነት ሆኖ እንጂ ለሰላም ቅድሚያ ትሰጣለች ብለዋል።

አሁንም የሰላም ችግር የሚፈጥሩ እንቅፋቶች ከተወገዱ የሰላምን መንገድ የማትመርጥበት ምክንያት የለም ብለዋል።

የኦባሳንጆን ጥረት ጨምሮ የኢትዮጵያን ሰላም በማሰብ ተደራደሩ የሚሉ ወገኖችን መንግስት ጥያቄ እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸው፤ የሰላም ሂደቱን በተመለከተም እያስረዳን ነው ብለዋል።

የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ከሁሉም አጀንዳዎች በላይ እንደሆነ ገልጸው፤ መንግስት ወደ ሰላም ድርድር የሚያስቀምጣቸው ቅደመ ሁኔታዎች እና አጀንዳዎች በኋላ የሚወሰን ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከአንድ ማዕከል የሚፈሱ የሚመስሉ በውሸት የተቀናበሩ ዘገባዎች እያቀረቡ መሆኑንም ነው አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተናገሩት፡፡

ለአብነትም "አዲስ አበባ ተከቧል"፤ "ኢትዮ-ኬንያ ድንበር ተዘግቷል" የሚሉና ሌሎች መሰል ሐሰተኛ መረጃዎችን በተቀናጀ መልኩ ሲያሰራጩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በሚመለከት በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት እያሰራጩ ያሉትን ሐሰተኛ መረጃ በማውገዝ ሰልፍ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

በተመድና ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኞቼ ታስረውብኛል የሚለውን ስሞታ በተመለከተ ማንም የዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኛ የኢትዮጵያን ህግ ማክበር ግዴታ እንዳለበትም አንስተዋል።

የአገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማክበር ካልቻለ ማንም አካል ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም