ቀጥታ፡

በኢትዮጵያን ያለውን ነባራዊ ሃቅ ለመላው ዓለም ለማሳወቅ ሰፊ ተደራሽነት ባላቸው ቋንቋዎች መረጃዎችን ማድረስ ይገባል

አዲስ አበባ ህዳር 01/03/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያን ያለውን ትክክለኛ እውነታ ለመላው ዓለም ለማሳወቅ ሰፊ ተደራሽነት ባላቸው ቋንቋዎች መረጃዎችን ማድረስ እንደሚገባ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ምሁራን ተናገሩ።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በካደ መልኩ የተሳሳተ ዘገባ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ላይ አፈሙዝ አንስተው ከተሰለፉ አሸባሪዎች በተጨማሪ በተለይም አንዳንድ የምእራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ ማይካቸውን አንስተው የጥፋት ዘመቻቸውን ከፍተዋል።

እነዚህን የጥፋት መልእክተኞች የሃሰት መረጃ በማጋለጥ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታው ለመላው ዓለም ተደራሽ ለማድረግ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ለዘመቻው ሊሰለፉ እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነትና ተግባቦት እየሰሩ የሚገኙት ሃይማኖት ጌታቸው፤ ከኢዜአ ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት በተለያዩ አውደ ግንባሮች የተከፈቱብንን ውጊያዎች ለማሸነፍ የሁላችንንም መሰለፍ ይጠይቃል።

ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ያላቸው ሲ ኤን ኤን፣ ቢቢሲ  እና ሌሎችም መገናኛ ብዙሃን ከጋዜጠኝነት  መርህ በወጣ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ የውሸት መረጃ እያሰራጩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለማንም ሳይወግኑ መዘገብ ከጋዜጠኝነት መርህ አንደኛው ቢሆንም ለጋዜጠኝነት መርህ ቆመናል የሚሉት እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ለአሸባሪው ህወሃት በመወገን መርሁን ጥሰው እየሰሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በመሆኑም በኢትዮጵያን ያለውን ትክክለኛ እውነታ ለመላው ዓለም ለማሳወቅ ሰፊ ተደራሽነት ባላቸው ቋንቋዎች መረጃዎችን ማድረስ ይገባል ብለዋል።

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የአንድ ወገን የተሳሳተ መረጃ እንዳይዝ የተለያየ የቋንቋ ችሎታ ያላቸው ምሁራን የአገራቸውን እውነታ የማሳወቅ ሃላፊነት አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል።

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር በውቀት ሲሳይ፤ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን መሰረታዊ የጋዜጠኝነት መርህን በመጣስ በኢትዮጵያ ላይ የጥፋት ዘመቻ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

አንዳንዶቹ በተጨባጭ ያልተረጋገጠ መረጃን ሲያቀርቡ እንደሚስተዋሉ ጠቅሰው በቅርቡ ሲ ኤን ኤን ያሰራጨውን መረጃ ለአብነት አንስተዋል።

የቴሌቪዥን ጣቢያው የአሸባሪውን ህወሃት የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በመቀበል በማስተጋባት በግልጽ መወገኑን አሳይቷል ብለዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪ ቢለኔ ስዩም ከሲ ኤን ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ማስረዳታቸውን አስታውሰው የሚዲያው አካሄድ ግን ሚዛኑን የሳተ መሆኑን መምህር በውቀት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ያስተላለፉትን መልእክት ሲ ኤን ኤን የተዛባ ትርጉም በመስጠት መግለጹ ሚዲያው የኢትዮጵያን እውነት በቅጡ ለመረዳት ዝግጁ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ሰሞኑን ቢለኔ ስዩም ወደ ሚዲያው ቀርበው እውነቱን ያስረዱበትን አካሄድ መከተል የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የያዘውን እውነታ ለአለም ለማድረስ በምሁራን በኩል የተጀመሩ ጥረቶች እንዳሉ ጠቅሰው ይበልጥ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የተለያዩ የመረጃ አውታር ማግኘት የሚችል ሁሉ የአገሩን እውነትና የአሸባሪውን ህወሃት ግፍ ለማጋለጥ ይስራ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም