ቀጥታ፡

በአዲስ አበባና አካባቢው የአሸባሪውን ቡድን ተልዕኮ ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ በርካታ ተጠርጣሪዎችና ጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ህዳር 1 /2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባና አካባቢው የአሸባሪውን ቡድን የሽብር ተልዕኮ ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ በርካታ ተጠርጣሪዎችና ጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የመዲናዋ የጸጥታ ግብረ ሃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ዛሬ ማምሻውን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት በወንጀል መከላከልና ምርመራ ዘርፍ በመዲናዋ በርካታ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ግፎችን እየፈጸመ ያለው አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ሸኔን ጨምሮ የተለያዩ ፀረ ሰላም ኃይላትን በማደራጀት የሽብር ተልዕኮውን ለማስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ከሸኔ ጋር በመተባበር የሽብር ተልዕኮውን በማስፋፋትና የአገር ህልውናን አደጋ ላይ ለመጣል እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም በመዲናዋና አካባቢዋ የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል ሌት ተቀን እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ግብረ ሃይሉ ባደረገው አሰሳና ፍተሻም የሽብር ቡድን የመለመላቸው የሽብር ተልዕኮ የተቀበሉ በርካታ ተጠርጣሪዎች እንዲሁም የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎችና ተተኳሾች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በተለያዩ ተቋማት የተሰገሰጉ እና በአካባቢው ሽብር የሚነዙ ፀጉረ ልውጦች ከነሀሰተኛ መታወቂያቸው መያዛቸውን፤ የጎዳና ተዳዳሪ በመምሰልና በቤተ እምነቶች በፀበል ቦታ የሀይማኖት አባትና ፀበልተኛ በመመሰል የገቡ ተልዕኮ ወስደው የተሰማሩ ግለሰቦች በአሰሳ ተይዘው ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተካሄደው የፍተሻና ብርበራ ኦፕሬሽን የመከላከያን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ፀጥታ ኃይላት አልባሳት፣ ማዕረግና መለዮዎች፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ ኮምፓስ፣ ጂፒየስ፣ ተተኳሽ የቡድኑ መሳሪያ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ገንዘቦች ይገኙበታል።

ለሽብር ተልዕኮ የሚያገለግሉ የሳተላይት ስልኮች፣ ሬዲዮ፣ ገመድ አልባ ስልኮች፣ ላፕቶፖች፤ የፎቶ ካሜራዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በፍተሻው ከተያዙ የጦር መሳሪያዎችና ተተኳሾች በተጨማሪ የተለያዩ ፈንጅና መሰል ነገሮችን በፔስታል እየተጠቀለሉ በጎዳና ላይ ተጥለው መያዛቸውን ገልጸዋል።

ሀሰተኛ መታወቂያ የሚያዘጋጁ አካላትም ከማተሚያ መሳሪያዎቻቸው ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል።

‘የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ታስረዋል’ የሚለውን መረጃ በተመለከተ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በወንጀል የተጠረጠሩ እንጂ ከድርጅት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ገልፀዋል።

አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ ማንኛውም የውጭ ዜጋ ስጋት ሊኖረው እንደማይገባ ይልቁንም ጥብቅ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን ገልፀው፤ “በአንዳንድ ሚዲያዎች በዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ላይ መዋከብ እንዳለ የሚገለፀው የተዛባ መረጃ ነው” ብለዋል።

በቪየና ስምምት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በስተቀር ማንኛውም በተለያዩ ወንጀል የተጠረጠረ አካል የሌላ አገር ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ዜጋ በአገሪቱ ህግ መሰረት እንደሚያዝ አስገንዝበዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በተከለከሉ ተግባራት የሽብር ኃይሉን በመደገፍና አገር በማፍረስ ተልዕኮ የተሰማሩ እንጂ በዘር፣ በብሔር፣ በዜግነት ወይም በሚሰሩበት ቦታ ማንነት እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በሰሞኑ በቁጥጥር ስር የዋሉ የውጭ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦችም የአገር ሉዓላዊነት በሚያዛቡ ወንጀሎች ቀጥታ ግንኙነት እንዳላችው ተጠርጥረው እንጂ በተመድ ተቋማት ላይ በቀጥታ የተሰራ ኦፕሬሽን እንደሌለ ገልጸዋል።

ዳያስፖራ ሆነው ተልዕኮ ይዘው የመጡና ሽብር የሚሰሩና የሚያሰሩ ኃይሎች መያዛቸውን ጠቁመዋል።

የመከላከያ፣ ፖሊስ፣ መረጃና ደህንነት፣ ኦሮሚያ ፖሊስና ሪፐብሊካን ጋርድ 24 ሰዓት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ለተጠርጣሪዎቹ መያዝ የህብረተሰብ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀው፤ አሁንም በአካባቢውና በሚንቀሳቀስበት አካባቢ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ጥቆማውን እንዲቀጥልና አገርና ህዝብን ከሽብር ቡድኑ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።

ማንነታቸው የማይታወቅ የሸኔ አባላት በጥበቃና መሰል ስራዎች የሚሰማሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ግለሰቦቹን መታወቂያ መጠየቅና ጥቆማ መስጠት እንዳለባቸው ጠይቀዋል።

በአዋጁ መሰረት የፖሊስ እርምጃዎችን በተመለከተ አንዳንድ የአገር ውስጥና የውጪ ሚዲያዎች በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ አድርገው የተዛባ መረጃ እያሰራጩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

አንዳንድ የፖሊስ አባላት የስነ-ምግባር ችግር እንዳለባቸው ህብረተሰቡ በተለያየ መንገድ በሰጠው ጥቆማ መሰረት በተደረገ ማጣራት በትናንሽ ጥቅም የተደለሉ ጥቂት የጸጥታ አካላት ተይዘው በየደረጃው እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ተጠርጣሪዎችን በመጠቆምና በማጋለጥ ላበረከተው አስተዋፅኦ በአንዳንድ መልካም ስነ-ምግባር በጎደላቸው የጸጥታ አባላት ምክንያት ተስፋ ሳይቆርጥ ከፖሊስና ከሌሎች የደህንነትና የፀጥታ አካላት ጎን በመሆን እየሰጠ ያለውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም