ቀጥታ፡

አዋጁ አሸባሪውን ህወሓትና ግብረ አበሮቹን ከሕዝብ ነጥሎ በማውጣት የአገርና የሕዝብን ደህንነት ያስጠብቃል

ህዳር 1/2014 /ኢዜአ/የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሸባሪውን ህወሓትና ግብረ አበሮቹን ከሕዝብ ነጥሎ በማውጣት የአገርና የሕዝቡን ደህንነት እንደሚያስጠብቅ የሕግ ባለሙያዎች ገለጹ።
የዜጎችን ደህንነትና የአገር ሕልውና ለማስጠበቅ የፀጥታ አካላትና ሕዝቡ በመቀናጀት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጤታማነት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በቅርቡ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች አዋጁ ኢትዮጵያ የተስማማችባቸውን ዓለምአቀፍ ስምምነቶችና መብቶች እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን ያማከለ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠበቃና የሕግ አማካሪ ፋሲል ስለሺ ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር ሕገ መንግስቱንና አገር የሚያፈርስ፤ የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ አዋጁ አስፈላጊና ችግሩን ለመፍታትም ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሩና ለደህንነቱ በአንድነት እንዲቆም የሚያደርግና በውጭና በውስጥ ያሉ የሽብር ሃይሎችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ያሉት ደግሞ ጠበቃና የሕግ ባለሙያ ወንድሙ ኢብሳ ናቸው።

ኢትዮጵያ ባለፉት 153 ዓመታት በተለያዩ ሃይሎች ወረራዎች ገጥመዋታል ያሉት ጠበቃ ወንድሙ  'ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እገባለሁ' የሚል ወረራ ግን በታሪኳ ገጥሟት አያውቅም ብለዋል።

ይህ ድርጊት ኢትዮጵያዊያንን ያስቆጣ መሆኑንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁም እንደ አገር አስፈላጊና አማራጭ የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።

የሕግ ባለሙያዎቹ አዋጁ አገርና የዜጎችን ህልውና ለማዳን የወጣ እንደመሆኑ የፀጥታ አካላትና ዜጎችም ለተፈፃሚነቱ በቅንጅትና በንቃት መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በተለይ አገር ለማፍረስ ከተነሳው ህወሓት ጋር የሚያብሩና የሚደግፉ ተጠርጣሪዎችን መጠቆም የዜጎች  ሃላፊነት መሆኑን የተናገሩት ጠበቃና የሕግ አማካሪ ፋሲል ስለሺ ናቸው።

ዜጎች አዋጁ ያለአግባብ ሲተገበር ከተመለከቱም በመረጃ ላይ በመመስረት ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ መብት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

ጠበቃና የሕግ አማካሪ ወንድሙ ኢብሳም አዋጁ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የፀጥታ ሃይሉ ከሕዝቡ ጋር በቅርበት በመስራት ተጠርጣሪዎችን ከንፁሃን መለየት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

ይህ ከሆነ አሸባሪዎች ወደ ሕግ የሚቀርቡበትና የአገር ሕልውና የሚረጋገጥበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን አክለዋል።

በተጠርጣሪዎች ላይ የሠብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይኖርና ሌሎች መጣስ የሌለባቸው ሕግጋትም እንዲከበሩ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም