ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሐሰት መረጃ ዘመቻ የሚቃወም ሠላማዊ ሰልፍ በካናዳ ቶሮንቶ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሐሰት መረጃ ዘመቻ የሚቃወም ሠላማዊ ሰልፍ በካናዳ ቶሮንቶ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ህዳር 1/2014 (ኢዜአ) ምዕራባዊያን አገራትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የሐሰት መረጃ ዘመቻ የሚቃወም ሠላማዊ ሠልፍ ከነገ በስቲያ በካናዳ ቶሮንቶ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
'የኢትዮጵያዊያን ማኅበር በቶሮንቶና አካባቢው' አባል ጋዜጠኛ ብርሃኑ ተክለሚካኤል ሠላማዊ ሠልፉ ከነገ በስቲያ ሕዳር 3 በኢትዮጵያዊያን ሠዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3፡00 ሠዓት ጀምሮ በካናዳ ቶሮንቶ በሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ እንደሚካሄድ ለኢዜአ ገልጿል።
በሠላማዊ ሠልፉ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሌሎች ምዕራባዊያን አገራትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በተቀናጀ መልኩ ኢትዮጵያን አስመልክቶ እያሰራጩት ያለውን ሀሰተኛ መረጃ እንዲያቆሙ ጥሪ እንደሚቀርብ ተናግሯል።

ሠልፈኞቹ የካናዳ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና የካናዳው ዕለታዊ ጋዜጣ ቶሮንቶ ስታር ሰንን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እያወጡ ያለውን ሀሰተኛ መረጃ እንደሚቃወሙም አመልክቷል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊትና ያደረሰውን ውድመትም ያወግዛሉ።
"ምዕራባዊያን አገራት ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ"፣ "ምዕራባዊያን አገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማክበር አለባቸው"፣ "ኢትዮጵያ የማንንም ጣልቃ ገብነትና ጫና አትቀበልም"፣ "ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ናት፤ አሁንም ሉዓላዊነቷ ተከብሮ ይቀጥላል" እና "ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እያሰራጩ ያሉትን የሐሰት መረጃዎች ያቁሙ" የሚሉ መልዕክቶችም ይተላለፋሉ።
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም የሚያሳስብ ደብዳቤ በቶሮንቶ ለሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ እንደሚሰጥም ጋዜጠኛ ብርሃኑ ገልጿል።
ሠልፉ ዳያስፖራው የአገር ሕልውና ዘመቻውን በመደገፍ ከመንግሥት ጎን መቆሙን የሚያሳይበት እንደሆነም ተናግሯል።
በሠላማዊ ሠልፉ ላይ ለኢትዮጵያ እየተሟገቱ የሚገኙት ካናዳዊው ጋዜጠኛ ጄፍ ፒርስና በካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጌራልድ እንደሚገኙ ይጠበቃል ሲል ጠቁሟል።
በሠልፋ ላይ በካናዳ የተለያዩ ግዛቶችና ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች የሚሳተፉ ሲሆን በካናዳ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ተወካዮች ንግግር ያደርጋሉ።
ጋዜጠኛ ብርሃኑ "በካናዳ የሚገኘው የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ልዩነቶቹን ወደ ጎን ትቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር ለማስጠበቅ በጋራ ቆሟል" ብሏል።
በካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የአገሪቷን መልካም ገጽታ የማስጠበቅና የሀሰት መረጃዎችን የማክሸፍ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙና ይህም ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጿል።
በካናዳ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በቀጣይ የምዕራባዊያን አገራትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙና የአገር ሕልውና ዘመቻውን የሚደግፉ መርኃ ግብሮች እንደሚያዘጋጁም ጠቁሟል።