የምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀን የሀሰት ዘገባዎች እናጋልጣለን - ኢዜአ አማርኛ
የምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀን የሀሰት ዘገባዎች እናጋልጣለን
ሚዛን አማን ህዳር 1/2014 /ኢዜአ/የምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀን ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያሰራጯቸውን የሀሰት ዘገባዎች ለማጋለጥ ሙያቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች አስታወቁ።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ስለሀገራቸው ዕውነታ በዘመቻ በመስራት ለምዕራባዊያኑ መገናኛ ብዙሃን የሀሰት ዘመቻ ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚገባቸው አንድ የዘርፉ ምሁር አመልክተዋል።
ህዝቡ ሀሰተኛ ዘገባዎችን እንዲረዳ ከማድረግ ባለፈ ትክክለኛ መረጃዎችን ቀድሞ እንዲያገኝ በማድረግ ሙያዊ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የፋና ብርድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ ተስፋዬ ምሬሳ እንዳለው ቢቢሲ፣ ሲ.ኤን.ኤን እና መሰል መገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ጉዳይ እያሰራጩ ያሉት "የበሬ ወለደ" ሀሰተኛ ዘገባዎች ለአሸባሪው ህወሓት ያላቸውን ወገናዊነት በግልጽ ያሳየ ነው።
ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን ከቻሉ ማፍረስ ካልቻሉ ደግሞ መንግስቷ አቅመ ቢስ እንዲሆን ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት በመገኛኛ ብዙሀን ዘዴዎቻቸውና በህወሓት በኩል እያንጸባረቁ መሆናቸውን አመልክቷል።
መገናኛ ብዙሀኖቻቸው ተናበው ተመሳሳይ የፕሮፓጋንዳ ዘገባ እየሰሩ መሆናቸውን ጋዜጠኛ ተስፋዬ ተናግሯል።
ምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀኖቻቸውን በመጠቀም በሚያሰራጯቸው ሐሰተኛ ዘገባዎች በዓለም ላይ ጥቂት የማይባሉ ሀገራትን ለመበታተን መቻላቸውን የገለጸው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ኢትዮጵያ ላይም ተመሳሳይ ዘመናዊ የጥቃት ዘመቻ በመክፈት ለአሸባሪው ወግነው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክቷል ።
የጋዜጠኝነት መርህ ያልተከተለና ሚዛናዊ ያልሆነ መረጃ በማቀበል ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሀንን ህዝቡ እንዲያውቃቸው እየሰራን ነው " ያለው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ሙያው በሚፈቅደው ሁሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለማጋለጥና ለመቀልበስ እንደሚሰራ አስታውቋል ።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የእጅ ስልኩን እንደመሳሪያ በመጠቀም በማህበራዊ የትስስር ገጾች ሴራቸውን ማክሸፍ እንዳለበት አስገንዝቧል።
የደቡብ ሬድዮና ተሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኛ ጦያር ይማም በበኩሉ "የጋዜጠኝነት መርህን ተከትለው ይሰራሉ ተብለው እንደማሳያ የሚጠቀሱ የምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀን ዘዴዎች በዚህ ደረጃ ወርደው ሐሰተኛ ዜና ሰርተው መገኘታቸው የሚያሳፍር ነው" ብሏል።
"መገናኛ ብዙሀኑ ከእውነት እጅግ የራቀ መረጃ ለዓለም ህዝብ በማድረስ ኢትዮጵያ ላይ መጥፎ ምስል እየፈጠሩ ይገኛሉ" ብሏል።
"መገናኛ ብዙሀኑ ለፖለቲካ ዓላማ እንጂ ገለልተኛ ሆነው ለህዝብ መረጃ ለመስጠት እንዳልተቋቋሙ በሚሰሯቸው የሀሰትና ግጭት አባባሽ ዘገባዎች ተለይተዋል" ሲል አክሏል።
የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያናና ሌሎች በርካታ ችግር ላይ የወደቁ ሀገራት የምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀን የሀሰት ዘገባ ሰለባዎች ስለመሆናቸው ሰሞኑን ኢትዮጵያ ላይ ከከፈቱት ዘመቻ መረዳት እንደሚቻል አመልክቷል።
የመገኛኛ ብዙሀኑ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያሰሯጯቸውን የሀሰት ዘገባዎች ተከታትሎ በማጋለጥና ትክክለኛና እውነታ አዘል የሆኑ ዘገባዎችን ፈጥኖ በማሰራጨት ሙያዊ ሀላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቋል ።
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህርት ማርች አየነው በበኩላቸው ሀሰተኛ ዘገባ መጥፎ ገፅታ ለማስያዝ ሆን ተብሎ፣ አልያም ባለማወቅ የተሳሳተ መረጃ በማስተላለፍ የሚፈጠር መሆኑን ተናግረዋል።
የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሀን ከሰሞኑ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያሰሯጯቸው ዘገባዎች ከአንድ ወገን ብቻ በተወሰደ መረጃ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል ።
"እንዲህ ያለው አሰራር ትክክል ካለመሆኑ ባለፈ እውነትን ለመደበቅ ምሉዕ ያልሆነ ምንጭ ስለመጠቀማቸው ያሳያል" ብለዋል።
"ትልቅ የሚባሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዜዴዎች የሚያሰራጯቸውን ዘገባዎች ህብረተሰቡ ፍጹም አድርጎ የሚቀበል ቢሆንም እንኳ ውስጣቸው ሲፈተሽ ብዙ ችግር አለባቸው " ሲሉ አክለዋል።
ኢትዮጵያዊያን መገናኛ ብዙሀን ዘዴዎቹ የሚያሰራጯቸውን ሀሰተኛ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን በተለያየ መንገድ ባለማጋራትና ባለማስፋፋት እንዲሁም እውነታን የተላበሱ መረጃዎችን አጉልቶ በማሰራጨት ሀገር የማፍረስ ሴራቸውን መመከት ይገባናል" ሲሉ መምህርቷ መክረዋል።
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ስለሀገራቸው ዕውነታ በዘመቻ በመስራት ለምዕራባዊያኑ መገናኛ ብዙሃን የሀሰት ዘመቻ ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።