አዋጁ ህዝቡን ከስጋት የሚያወጣና ወቅቱን የጠበቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዋጁ ህዝቡን ከስጋት የሚያወጣና ወቅቱን የጠበቀ ነው

አዳማ ፤ ህዳር 1/2014 (ኢዜአ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሀገርን ሰላም በማስከበር ህዝቡን ከስጋት የሚያወጣና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ገለጹ።
የአዳማ ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ ሃጂ ሁሴን ሃሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አዋጁ የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በአግባቡ ለመለየት አሁን እየደረሰ ያለውን ችግር ለመከላከል ወሳኝ ነው።
ፀጥታን ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ ከመሆኑም ባለፈ ህዝቡን ከስጋት እንደሚያወጣም ነው የተናገሩት።
በተለይ የዜጎች ህይወትን ለመታደግና የሀገር ህልውና ለማስከበር ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።
"አሸባሪው እየፈፀመ ያለው ድርጊት በሀገራችን ታሪክ ሰምተንም አይተንም የማናቀው ለመስማት የሚዘገንን ነው" ያሉት ሃጂ ሁሴን፤ የንፁሃን ዜጎች ህይወት እያጠፋ ያለ አረመኔ ቡድን መሆኑን ገልጸዋል።
የቱለማ አባገዳ ለማ ቱምሳ በበኩላቸው፤ ሀገራችንን ለማፍረስ ከውጭ ሃይሎች ተልዕኮ በመቀበል የፖለቲካ ቁማር በኢትዮጵያ ላይ እየተጫወቱ ያሉ አካላትን ለመቆጣጠር አዋጁ የጎላ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
ህዝቡን እያወናበዱ ያሉ አጭበርባሪ አካላትን መከላከል እንደሚገባ አመልክተው፤ "እኛ እንደ አባገዳ ህብረተሰቡ ተደራጅቶ የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው"ብለዋል።
ወጣቱ የጥፋት ሃይሎች መሳሪያ እንዳይሆን ቄሮና ቀሬዎች ለሀገራቸው ዘብ እንዲቆሙ እየመከርን እያስተካከልን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አዋጁ አንገታችን ቀና እንዳናደርግ ባለፉት 27 ዓመታት በደል የፈጸመብን አሸባሪውን ሕወሓትና ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር ብሎም ባሉበት ለመደምሰስ ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የአዳማ ወረዳና አዳማ ከተማ አባገዳ ሮባ ቡኔ ናቸው።
ወጣቶቻችን የጥፋት ሃይሎች መሳሪያ እንዳይሆኑና በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን በአንድነት ቆመን አሸባሪውን ቡድን እናስወግዳለን፣ ወጣቶቻችን ለሀገር መከላከያ ደጀንና ጉልበት እንዲሆኑ እያደረገን ነው ብለዋል አባገዳ ሮባ።