ቀጥታ፡

ሐሰተኛ ዘገባዎችን በእውነተኛ ዘገባዎች መመከት ይገባል

ህዳር 01/2014(ኢዜአ)  በሐሰተኛ ዜናና በስም ማጥፋት ተቀናጅተው እየሰሩ ያሉት የምዕራባዊያን ዘገባዎች ጆሮ አለመስጠትና በእውነተኛ ዘገባዎች መመከት እንደሚገባ በኢትዮጵያ የፓክስታንና የደቡብ ሱዳን አምባሳደሮች ገለጹ።

ፓኪስታንና ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አምባሳደሮቹ ገልጸዋል።

ዕውቅናን ያተረፉ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ከጋዜጠኝነት ስነ ምግባር መርሆና ህጉ ውጭ ለአንድ ቡድን ፍላጎት የወገኑ የሐሰት ዘገባዎችን በኢትዮጵያ ላይ ሲነዙ ተስተውለዋል።

ለአብነትም የአሜሪካው ግዙፉ የቴሌቭዥን ጣቢያ ሲኤንኤን ከሰሞኑ አዲስ አበባ በታጣቂዎች ተከባለች፣ ሰላም የለምና የውጭ ሀገር ዜጎች ከተማዋን ለቃችሁ ውጡ የሚል የበሬ ወለደ ሀሰተኛ ዘገባዎችን አሰራጭቷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኦሮሚያ የብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ከፓክስታንና ደቡብ ሱዳን አምባሳደሮች  ጋር ቆይታ አድርጓል።

በኢትዮጵያ የፓክስታኑ አምባሳደር ሸዛብ አባስ በቆይታቸው ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ሀገር የውስጥ ችግር እንዳጋጠማት ገልጸው፤ ይሄንንም ለመቆጣጠር እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል።

ሀገራቸው በማንኛውም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ የገለጹት አምባሳደር ሸዛብ፤ የውጭዎቹ ሚዲያዎች ከሚነዙት የሐሰት ዜና ይልቅ ሀገሪቷ ያላትን እውነት በማሳየቱ ላይ ልታተኩር ይገባል ብለዋል።

የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ እያሰራጩ ያለውን የሐሰት ዘገባ የሀገሪቷ ሚዲያዎች ባላቸው እውነታ ሊያሸንፉ ይችላሉም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒሺያ ሞርጋን በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን ለውጭ ሚዲያዎች አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ጆሮ መስጠት እንደማይገባቸው ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የራሷ ጉዳይ ስለሆነ በራሷ እንድትፈታ መተው ነው ያለብን፤ ምናልባት ግን ለእገዛ ከጠየቀችን በቅንነት መርዳት ያለና የነበረ ነው ብለዋል አምባሳደሩ።

መርሳት የሌለብን ግን በማለት ያከሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ከራሷ ጉዳይ አልፋ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለማሸማገል የሚያስችላት በቂ ልምድ ያላት፤ የተመድ እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች እንደነበረች ለአብነት አንስተዋል አምባሳደሩ።

ፓክስታንና ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን ታሪካዊ ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት አምባሳደሮቹ፤ በቀጣይም ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም