በጋምቤላ የማጃንግ ዞን ህዝብ አሸባሪው ህወሃት ሀገር ለማፍረስ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመመከት ልጆቹን እያዘመተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ የማጃንግ ዞን ህዝብ አሸባሪው ህወሃት ሀገር ለማፍረስ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመመከት ልጆቹን እያዘመተ ነው
ደብረ ብርሀን ፤ ህዳር 1/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የማጃንግ ብሄረሰብ ዞን ህዝብ አሸባሪው ህወሃት ሀገር ለማፈረስ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመመከት ልጆቹን መርቆ በመሸኘት እያዘመተ መሆኑን የዞኑ ዋና አሰተዳዳሪ አስታወቁ።
የዞኑ ህዝብ በአሸባሪው ቡድን ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች ዛሬ 3 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የማጃንግ ብሄረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሀም ማይክል ፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራና አፋር ህዝቦች ላይ የፈፀመው ግፍ በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ጥቁር ጠባሳ መሆኑን ገልጸዋል።
የዞኑ ህዝብ አሸባሪው ህወሃት ሀገርን ለማፈረስ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመመከት ልጆቹን መርቆ በመሸኘት እያዘመተ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ቡድኑን ደምስሶ ለኢትዮጵያ ዳግም ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ከማድረስ ጎን ለጎን በጥቃቱ የተጎዱ ዜጎችን መደገፍ የግድ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም በአሸባሪው ቡድን ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ ወገኖች ከማጃንግ ብሄረሰብ ዞን ህዝቡ የተዋጣ 733 ኩንታል በቆሎ እና 3 ሺህ 200 የተለያዩ አልባሳት ዛሬ ድጋፍ መደረጉን አቶ አብርሀም ገልጸዋል።
የተደረገው ድጋፍ 3 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ግምት እንዳለው ጠቅሰው፤ የሀገሪቱ ሰላም ተረጋግጦ ዜጎች ወደ መደበኛ ስራቸው እስኪመለሱ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።
የማጃንግ ብሄረሰብ ዞን ህዝብ ተወካይ ሼህ ሰይድ አህመድ፤ ይህ ወቅት ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ የምንረዳዳበትና የምንተጋገዝበት ትክክለኛ ጊዜ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መዥገር የሆነው አሸባሪው የህወሃት ቡድን እስኪደመሰስና የሀገሪቱ ሰላም እስከሚረጋገጥ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ቡድን በፈጠው ችግር ከሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች የተፈናቀሉ 218 ሺህ 955 ወገኖች በዞኑ የተለያዩ ጊዜያዊ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
''እነዚህ ወገኖች ከነበራቸው ሀብትና ቤት ተፈናቅለው ለጋስና አምራች እጃቸው ለእርዳታ ተዳርጎ ከማየት በላይ ህመም የለም'' ብለዋል።
በጋምቤላ ክልል የማጃንግ ብሄረሰብ ዞን ህዝብ ችግሩን በመረዳት ፈጥኖ ወገናዊ ድጋፍ ማድረጉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
ይህ አስቸጋሪ ወቅት እስኪያልፍ ሌሎች ወገኖችም ለእነዚህ ሳይበድሉ ለተበደሉ ንፁሃን ወገኖች የድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።
በድጋፍ ርክክቡ ሥነ-ሥርዓት የማጃንግ ብሄረሰብ ዞን እና የሰሜን ሸዋ ዞን አመራሮች እንዲሁም የህዝብ ተወካይና ባለድረሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡