"የኢትዮጵያ እውነት የማይዋጥላቸው ሰዎች ባይወዱትና ባይፈልጉትም እውነቱን መናገሬን እቀጥላለሁ" - ኢዜአ አማርኛ
"የኢትዮጵያ እውነት የማይዋጥላቸው ሰዎች ባይወዱትና ባይፈልጉትም እውነቱን መናገሬን እቀጥላለሁ"

ህዳር 1/2014/ኢዜአ/ "የኢትዮጵያ እውነት የማይዋጥላቸው ሰዎች ባይወዱትና ባይፈልጉትም እኔ እውነቱን መናገሬን እቀጥላለሁ" ትላለች ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ።
ራሷን "ከተጽእኖ ነጻ" ጋዜጠኛ /Independent journalist/ ብላ የምትጠራው የ33 ዓመቷ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩትን ሀሰተኛ መረጃ ማጋለጧን እንደምትቀጥል ትናገራለች።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገችው ሄርሜላ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን እውነት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቀው ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው ብላለች።
እ.አ.አ በ1988 በአዲስ አበባ ነው የተወለደችው ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ፤ በውልደት የኢትዮጵያ ዜግነት አላት፤ አሳዳጊዎቿ አሜሪካዊያን በመሆናቸው በምዝገባ የአገሪቱን ዜግነት አግኝታለች።
በኤመርሰን ኮሌጅ በብሮድካስት ጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላት ጋዜጠኛዋ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ትንታኔ በመስጠት ላይ ትገኛለች።
የትግራይ ክልልን በተመለከተ በማነሳቸው ሀሳቦች የሚያስፈራሩኝና የሚቃወሙኝ በአብዛኛው አክቲቪስቶች ናቸው የምትለው ሄርሜላ "አክቲቪስቶቹ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችና በማውቃቸው ሰዎች በኩል እየመጡ ዛቻ ያደርሱብኛል" ብላለች።
"የኢትዮጵያ እውነት የማይዋጥላቸው ሰዎች የምናገረውን አይወዱትም፤ የማነሳቸውን ጥያቄዎች አይፈልጓቸውም፤ ነገር ግን እኔ ያለውን እውነት ነው የምናገረው ይሄንንም እቀጥልበታለሁ" ብላለች።
በከፍተኛ ሁኔታ የዘመቱብኝ አንዳንድ ሰዎች 'እንዴት እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችን ታነሺያለሽ?' በማለት ትችት ይሰነዝሩብኛል ስትልም ገልጻለች።
የሚሰራጩ የፕሮፓጋንዳ መረጃዎችን ማጋለጥ ተገቢ ነው የምትለው ሄርሜላ ለትግራይ ሕዝብ እንቆረቆራለን የሚሉ የትግራይ ማኅበረሰብ አባላት መነሳትና መጠየቅ ያለባቸው ጉዳዮች እያነሱ አለመሆኑን ተናግራለች።
ለትግራይ እንቆረቆራለን የሚሉ ሰዎች እውነት ለሕዝቡ የሚያስቡ ከሆነ ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው ያለችው ጋዜጠኛ ሄርሜላ፤ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ድምጽ እየተሰማ ነው ብላ እንደማታምን ገልጻለች።
ከትግራይ ክልል ከግለሰብ ታሪኮችና አስተያየቶች ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ወደ ጦርነት ለመላክ እንደሚገደዱና አንልክም ካሉ የበቀል እርምጃ እንደሚወሰድባቸው መናገራቸውን ገልጻለች።
ያለ በቂ ስልጠናና መሳሪያ ወደ ጦርነት የሚሄዱ ልጆችም ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን የሚያሳዩ ዘገባዎች እየወጡ እንደሚገኙ ጠቅሳለች።
የሚፈጸሙ በደሎችን አስመልክቶ የሚወጡ ዘገባዎች ጎልተው ሲሰሙ ሰዎች ሃሳባቸውን ይቀይራሉ ብላ እንደምታምንም ነው ጋዜጠኛ ሄርሜላ የተናገረችው።
በሌላ በኩል አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን አስመልክተው እያወጧቸው ያሉ ዘገባዎች "ትክክለኛና ሚዛናዊ ያልሆኑ እንዲሁም እውነታዎችን ገሸሽ ያደረጉ ናቸው" ስትል ገልጻለች።
"በትግራይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ተፈጽሟል፣ መንግስት እርዳታ እንዳይደርስ ገድቧል" በሚል ሀሰተኛ ዘገባዎችን ሲያሰራጩ መቆየታቸውንም ጠቁማለች።
መንግስት እርዳታ እንዳይገባ አለመከልከሉ በማስረጃ ከመረጋገጡ ባለፈ የህወሓት ቡድን የሠብዓዊ እርዳታውን ለጦርነት ማዋሉ ቢረጋገጥም ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን ይሄን ለመዘገብ ፍላጎት አላሳዩም ብላለች።
መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባዎቻቸው አንኳር የሚባሉ ጉዳዮችን በመተው ዘገባ መስራታቸው ዜናቸው ግማሽ እይታ ያለው እንዲሆን የሚያደርግና የሚኖረውም ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ገልጻለች።
ጋዜጠኛ ሄርሜላ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩትን ሀሰተኛ መረጃ ማጋለጧን እንደምትቀጥልም ተናግራለች።
በህወሓትና በደጋፊዎቹ ዘር ማጥፋት ተፈጽሟል፣ ረሃብ ለጦር መሳሪያነት ውሏል እየተባለ ሲገለጽ ቢቆይም በቅርቡ በኢትዮጵያ የሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠብዓዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ በጋራ ያወጡት ሪፖርት እውነት አለመሆኑ መረጋገጡንም አስታውሳለች።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ እየተረዳ መምጣቱንና ከሰሞኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የተሳተፈበት የአዲስ አበባው ሠልፍም በምዕራባዊያንና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው የሚተላለፉ ሀሰተኛ መረጃዎችን ያወገዙ መሆናቸውን ጠቅሳለች።
ዜጎች አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ማሰማታቸው ትክክለኛ ነገር እንደሆነና ይበልጥ በአገራቸው ጉዳይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ዕድል እንደሚሰጣቸው ገልጻለች።
ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን እውነት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ድምጻቸውን ማሰማታቸውን መቀጠል እንዳለባቸውና ሌላ አካል ድምጽ ይሆነናል ብለው መጠበቅ እንደሌለባቸውም አመልክታለች።
ጋዜጠኛ ሄርሜላ አሁን ያለው ሁኔታ አልፎ ኢትዮጵያዊያን ፊታቸውን ወደ ልማት የሚያዞሩበትና ወደ መደበኛ ሕይወታቸው የሚለሱበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ያላትን ተስፋም ገልጻለች።
ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ መቀመጫውን በኒውዮርክ ባደረገው የሲቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዜና አንባቢነትና ሪፖርተርነት እንዲሁም በካሊፎርኒያው ክሮን ቲቪ በሪፖርተርነት፣ በቪዲዮ ካሜራ ባለሙያና አርታኢነት ሰርታለች።