ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አሸባሪውን ሃይል በጀግንነት እየተፋለሙት ነው

ህዳር 1/2014/ኢዜአ/ የአያቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አሸባሪውን ህወሃት በጀግንነት እየተፋለሙት መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የዘንድሮ የአፍሪካ ወጣቶች ቀን  “ወጣትነቴ ለሀገሬ!” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበር መሆኑን ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

እለቱ ኢትዮጵያ በውጭና በውስጥ ጠላቶቿ በሉኣላዊነቷና በህልውናዋ ላይ የተከፈቱባትን ጦርነቶች ለመመከት ወጣቱ የሚያደርገውን ተጋድሎ በመዘከር ይከበራል ተብሏል፡፡

በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሰቃቂ ጥቃት የፈጸመውን አሸባሪውንና ከሃዲውን የህወሃት ቡድን ለመደምሰስ ወጣቱ ግንባር ቀደም ሆኖ ተሰልፏል ብሏል፡፡

የሽብር ቡድኑ በአገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱና በውጭ ከሚገኙ ሃይሎች ጋር ግንባር ፈጥሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል እጓዛለሁ ብሎ መነሳቱን ያስታወሰው መግለጫው አገር ወዳዶች ሁሉ እየመከቱት መሆኑን ጠቅሷል።

በተለይም ወጣቶች የአያቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም አሸባሪውን ሃይል በጀግንነት እየተፋለሙት መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ወጣቱ ለትውልድ የሚተላለፍና ለዘላለም የሚዘከር ታሪክ እየሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ መናገራቸውን መግለጫው ጠቅሷል።

በዲፕሎማሲው አውድም ወጣት ዲያስፖራዎች በዲጂታል ሚዲያው እየተሠራጨ ያለውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመመከት የጠላቶችን ዓላማና አጀንዳ በዓለም መድረክ ተቀባይነት እንዳይኖረው የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለወገን ጦር ደጀን በመሆን፣ ስንቅ በማቀበል እንዲሁም የአካባቢያቸውን ደህንነት ከጁንታው ተላላኪዎችና ሰርጎ ገቦች በመጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል የዘማች ቤተሰቦችን የደረሰ የእርሻ ሰብል በመሰበብሰብ እንዲሁም አሸባሪ ሃይሎች በከፈቱት ጦርነት የተፈናቀሉና በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ህጻናት፣ እናቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን እየተንከባከቡ ይገኛሉ፡፡

እንዲሁም ማህበረሰቡንና ተቋማትን በማስተባበርና ድጋፍ በማሰባሰብ አኩሪ ተግባር ሲፈጽሙ ቆይተዋል፤ አሁንም የድርሻቸውን እየተወጡ በመሆናቸው በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል ብሏል መግለጫው።

በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት እስከሚረጋገጥ የወጣቱ እንቅስቃሴ ወደ ፊትም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ተብሏል።

ለዚህም ደግሞ ወጣቱ መከላከያን በመቀላቀል፣ በመደገፍ፣ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም አካባቢውን በንቃት መጠበቅ አንዳለበት ተመልክቷል።

የአፍሪካ ወጣቶች ቀን እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ በመከበር ላይ ሲሆን ዘንድሮ በአፍሪካ ደረጃ ለ15ኛ ጊዜ “Defining the Future Today: Youth- Led Solutions for Building the Africa We Want” በኢትዮጵያ ደግሞ “ወጣትነቴ ለሀገሬ!” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል፡፡

በየአመቱ ህዳር “የወጣቶች ወር” በሚል መርህ ልዩ ልዩ እና ተከታታይነት ያላቸው ሁነቶችን በማዘጋጀት ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም