ቀጥታ፡

አዲስ አበባና አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመፍታት በ85 ሚሊዮን ዶላር የመልሶ ግንባታ ስራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣  ህዳር 01/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባና አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመፍታት በ85 ሚሊዮን ዶላር የመልሶ ግንባታና አቅም የማሳደግ ፕሮጀክት ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በ50 ኪ.ሜ ራዲየስ በሚገኙ ከተሞች ፕሮጀክቱ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።

በዚህም በመዲናዋ እና አካባቢው የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት በ85 ሚሊዮን ዶላር የመልሶ ግንባታና የአቅም ማሳደግ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ፕሮጀክቱ በኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮች እርጅና ምክንያት የሚስተዋለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግር ለመፍታት የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ከሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ የትራንስሚሽንና ዲስትሪቢዩሽን መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።    

ፕሮጀክቱ ቻይና ኤሌክትሪክ ፓወር ኢኩፕመንት ቴክኖሎጂ እና ቻይና ናሽናል ሄቪ ማሽነሬ ኮርፖሬሽን በተባሉ የቻይና ተቋራጮች እየተገነባ መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል።

ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ 85 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በጀት በብድር ተገኝቷል፡፡

ከዚህ ውስጥ 60 ነጥብ 64 ሚሊየን ዶላር ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና 24 ነጥብ 46 ሚሊየን ዶላር ከጃፓን መንግስት በብድር መገኘቱ ተገልጿል፡፡

ግንባታውን በሚያዚያ ወር 2014 ዓ.ም መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።

በፕሮጀክቱ 625 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታና 266 የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች ተከላ የሚከናወን ሲሆን አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ከ35 በመቶ በላይ መድረሱ በመግለጫው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም