የምዕራባዊያን አሁናዊ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ከምን የመነጨ ይሆን? - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራባዊያን አሁናዊ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ከምን የመነጨ ይሆን?
አዲስ አበባ፣ ህዳር 1/2014 (ኢዜአ) የምዕራባዊያን አሁናዊ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ከምን የመነጨ ይሆን?
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ አየር ኃይል ባልደረባ ብርጋዴር ጄነራል መስፍን ኃይሌ፤ የምዕራባዊያኑ የፖለቲካ አቋም ብዙ ጊዜ ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር ገጥሞ አያውቅም ይላሉ።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን የነጻነት ፈንጣቂ መሆኗን ተከትሎ ኢትዮጵያ የምዕራባዊያኑ ፍላጎት ፀርና ነገር ቆስቋሽ አድርገው እንደሚመለከቷት ያብራራሉ።
ይህም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ላለው ለቀይ ባህር ቀረቤታ መኖሩም በምዕራባዊያኑ ጥርስ ውስጥ እንዳስገባት ገልጸዋል።
በዚህም በቅድመ አድዋም ሆነ በድሕረ አድዋ በተደረጉ ጦርነቶች ምዕራባዊያን በቀጥታም ሆነ በወኪሎቻቸው በኩል ኢትዮጵያን ሲወጉና ሲያዳክሙ መኖራቸውን አንስተዋል።
በየዘመናቱ የኢትዮጵያን ኃብት ለመቀራመት ያልተሞከረ ነገር እንደሌለ ዳሩ ግን ከሕወሓት ከሃዲ ሃይሎች በስተቀር ሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥታት ለባዕዳን ፍላጎት ተገዝተው እንደማያውቁ አብራርተዋል።
አሸባሪው ቡድን ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የባንዳነት ዝምድና እና የጥቅም ተጋሪነት ከምዕራባዊያን ፍላጎት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ሁነኛ ወኪል አድርገው ይመለከቱታል ብለዋል።
በአንጻሩ ከምዕራባዊያን ጥቅም ጋር አብሮ የማይሄድ መንግሥት ከሆነ ያንን መንግሥት ለማፍረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለም ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ ተዳክማለች በሚል ሶማሊያ ወረራ በፈጸመችባት ወቅት አሜሪካንን ጨምሮ ለምዕራባዊያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ብትጠይቅም ባላችሁ ተዋጉ ብለው ኢትዮጵያን እንደከለከሉ ገልጸዋል።
በወቅቱ ከወራሪው የዚያድባሬ ጦር ጀርባ ምዕራባዊያኑ እንደነበሩ አስታውሰው ምክንያታቸው ደግሞ የኦጋዴን ግዛት ከኢትዮጵያ እጅ እንዲወጣ እና በግዛቱ ያለውን ማዕድን መጠቀም በማሰብ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ከጦርነቱ በፊት የአሜሪካ ኩባንያዎች በኦጋዴን ነዳጅ መኖሩን አረጋግጠው የተለያዩ ሰበብ በመፍጠር እንዳይወጣ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ የባዕዳን ተልዕኮ በራሳቸው ጥቅም ብቻ የተንጠለጠለ መሆኑን ገልጸዋል።
የወቅታዊው የምዕራባዊያን ጫናም የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት አውርደው በሚፈልጉት የመተካት አዙሪት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም ለማድረግ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት የሚቀናቀኑ ኃይሎችን አንድም በገንዘብ አልያም ደግሞ በሌሎች ሥልቶች የመደለል ነባር ታሪክ አላቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ሁለንተናዊ ጫናም ከዚህ የመነጨ መሆኑን ብርጋዴር ጄነራል መስፍን ያስረዳሉ።
ምዕራባዊያን ኢትዮጵያዊያን ሲከፋፈሉ እንጂ አንድ ሲሆኑ ትርፍ እንደሌላቸው ገልጸው፤ ባለፈው ሥርዓት ለራሳቸው ጥቅም በፌዴራሊዝም ስም ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ብዙ ስለመሞከሩ ገልጸዋል።
የአሁናዊው የሕወሓት ጦርነት በር የከፈተውም ይሄው መከፋፈል ውጤት መሆኑን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያዊያን ከርዕዮተ ዓለምና ኢኮኖሚ በፊት የጋራ አገር ስለሚያስፈልግ መንቃት አለብን ይላሉ።
ከዚህ የምዕራባዊያን ጫና መውጣት የሚቻለውም ከአድማስ ባሻገር ያለውን ትልቅ ስዕል በማየት ጠንክሮ በጽናት በመቆም መሆኑን ተናግረዋል።
የምዕራባዊያን ፍላጎት ኢትዮጵያን መከፋፈል ነው ያሉት ብርጋዴር ጄነራል መስፍን፤ ይህንን በመገንዘብ ሁሉም ለአገር አንድነት እንዲቆም ጠይቀዋል።
በተለይም የአገር ሕልውና ጉዳይ ከሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው የተደቀነውን የህልውና አደጋ በተባበረ ክንድ መመከት ይገባል ነው ያሉት።
ህዝብን በአግባቡ የመምራት፣ የማንቃትና የማደራጀት ተግባራት ከመንግሥት ይጠበቃልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የሕልውና አደጋ ለመመከት በተደረገው አገራዊ ጥሪ ለመሳተፍ እርሳቸውና ሌሎች የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት ጓዶቻቸው እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የቀድሞ ሠራዊት አባላት ለአገር የሚጠቅም ብዙ ልምድ፣ ሙያና እውቀት ያላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ወረራውን ለመቀልበስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የቀድሞ ሠራዊት አባላት የካበተ ልምድና እውቀታቸውን በማጋራት ለአገር ህልውና ዘመቻው ብሎም ይበልጥ የተጠናከረ ሰራዊት ለመገንባት የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቅሰዋል።