አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች አስገድዶ መድፈርና የዘረፋ ወንጀል ፈጽሟል- አምነስቲ ኢንተርናሽናል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች አስገድዶ መድፈርና የዘረፋ ወንጀል ፈጽሟል- አምነስቲ ኢንተርናሽናል
ህዳር 1/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወራራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የአስገድዶ መድፈርና የዘረፋ ወንጀሎች መፈጸሙን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አረጋገጠ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለአንድ ዓመት ያህል የዘለቀውን ግጭት አስመልክቶ አሳሳቢ ያለውን የምርመራ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በዚህም የሽብር ቡድኑ በወራረ በያዛቸው የአማራ አካባቢዎች በርካታ ሴቶችን ከመድፈሩ ባለፈ ዘረፋና የግፍ ድብደባ መፈጸሙን ሪፖርቱ ይፋ አደርጓል።
በተጨማሪም የአሸባሪው የህወሓት ታጣቂዎች ሴቶችን በቡድን ሆነው ልጆቻቸው ፊት አስገድደው መድፈራቸውን አምነስቲ በሪፖርቱ አስታውቋል።
የሽብር ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሴቶችና በእናቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን እየፈጸመ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ይህን የመንግሥት ተደጋጋሚ መረጃ ሲያጣጥል የቆየው አምነስቲ ኢንተርናሸናል ዘግይቶም ቢሆን ባደረገው ማጣራት ወንጀሉ በአስከፊ ሁኔታ መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ብሏል።
የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል በንፋስ መውጫ ከተማ ብቻ እናቶችን ልጆቻቸው ፊት ከመድፈሩ ባሻገር ሴቶችን በኃይል አስገድዶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መውሰዱንም ሪፖርቱ አረጋግጧል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሃፊ አግነስ ካላማርድ እንዳሉት በአሸባሪው የህወሓት ታጣቂዎች የተፈጸሙ አጸያፊ ድርጊቶች በጦር ወንጀል እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም የከፉ ወንጀሎች በሚል የሚያስጠይቅ ነው።
የጥቃቱ ሰለባ የሆነች አንድ እናት ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደገለጸችው የ 9 እና የ 10 ዓመት ልጆቿ እያለቀሱ እፊታቸው በህወሓት ታጣቂዎች በቡድን ተደፍራለች።
እንዲህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት የቡድኑን የጭካኔ ጥግ የሚያሳይ ነው ሲሉ ዋና ጸሃፊዋ ኮንነውታል።
ድርጊቱ ሥነ-ምግባር የጎደለው ብቻ ሳይሆን ቅንጣት ያህል ስብዕና የሌለው አረመኔያዊ ቡድን እንደሆነ ያረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላ የጥቃቱ ሰለባ የሆነች ሴት የህወሓት ታጣቂዎች ከደፈሯት በኋላ ራሷን ስታ እንደወደቀች ለአምነስቲ ተናግራለች። ሰዎቹ ጥቃት ካደረሱባት በኋላ ጌጣጌጦቿን ዘርፈው እንደወሰዱባት ገልፃለች።
የአማራ ክልል መንግሥት ለአምነስቲ እንደተናገሩት ህወሃት ከተማዋን በያዘው የዘጠኝ ቀን አገዛዝ ወቅት ከ70 በላይ ሴቶች በንፋስ መውጫ ከተማ መደፈራቸውን አስታውቋል።
ሪፖርቱ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ባለፈው ነሃሴ በአማራ ክልል ገብቶ በፈጸመው ጥቃት ላይ ያተኮረ መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል።