በባህር ዳር ለህልውና ዘመቻው ከ173 ሚሊዮን በላይ የሚገመት በገንዘብና በአይነት ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ለህልውና ዘመቻው ከ173 ሚሊዮን በላይ የሚገመት በገንዘብና በአይነት ተሰብስቧል
ባህር ዳር፣ ጥቅምት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለህልውና ዘመቻው የሚውል ከ173 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ በጥሬ ገንዘብና በአይነት መሰብሰቡን አስታወቀ።
መንግስት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ተከትሎ ተጨማሪ 20 ሺህ ኩንታል ደረቅ ሬሽን እየተዘጋጀ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊና የሀብት አሰባሳቢ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ወይዘሮ ብረሃን ንጉሴ በሰጡት መግለጫ ከተማ አስተዳደሩ የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ የበኩሉን እየተወጣ ነው።
የህልውና ዘመቻውን ለማሳካትም ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብና ከ23 ሺህ ኩንታል በላይ ስንቅ ለማዘጋጀት ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም ከ143 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብና ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው 15 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
የተሰበሰበው ጥሬ ገንዘብም በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ሌሎች የፀጥታ አካላት ድጋፍ ለማዋል መቻሉን ገልጸዋል።
ድጋፉ ከባለሃብቶች፣ ከመንግሥት ሠራተኛውና ከከተማው ማህበረሰብ የተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመው፤ የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የተሰበሰበውን የምግብ እህልም በጋይንት፣ በወሎ፣ በደባርቅ እና በእብናት ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ በማድረግ የእርስ በርስ የመረዳዳት ባህል እንዲጎለብት ተደርጓል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ተከትሎ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ተመላሽ ወታደሮችን፣ ሚሊሻዎችን፣ ፋኖዎችንና የግል መሳሪያ ያላቸውን ግለሰቦች በግንባር ማሰለፍ መቻሉን ገልጸዋል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።