ኢትዮጵያን ማዳን የህልውናችን ተቀዳሚ ጉዳይ አድርገን እየሠራን እንገኛለን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ማዳን የህልውናችን ተቀዳሚ ጉዳይ አድርገን እየሠራን እንገኛለን
ድሬዳዋ፣ ጥቅምት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪውን ህወሃት ከነተላላኪዎቹን ለመደምሰስ የሚካሄደውን ዘመቻ በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማዳን ተቀዳሚ ጉዳይ አድርገው እየሰሩ መሆናቸውን በድሬዳዋ አስተዳደር የኃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ አባገዳዎችና ዑጋዞች አስታወቁ።
በአስተዳደሩ የሚገኙት እነዚህ አካላት በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በድሬዳዋ ተወያይተዋል።
አገርና ሠላም የሌለው ሰው ምንም ስለሌለው አገርን መጠበቅ ቀዳሚ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል።
አገርን ለማዳን ከፀሎትና ምህላ በዘለለ አሸባሪዎችን ለመደምሰስ የሚደረገው ዘመቻ እንዲሳካ ግንባር ድረስ ተጉዘው እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
የወያኔ ወራሪ ኃይል ቤተ እምነቶችንና መስጂዶችን በማፈራረስና ንፁሃንን በመጨፍጨፍ ሰይጣናዊ ተግባራት እያከናወነ እንደሆነም አንስተዋል።
አገርን ለማፍረስ የተነሳን ቡድን ማጥፋት ሃጢያት ያለመሆኑን ገልጸው፤ እስከ ግንባር ድረስ በመዝመት መስዋዕትነት ለመክፈል ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
ዘመቻውን በገንዘብና በቁሳቁስ ለመደገፍ የቁሳቁስና የገንዘብ ማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አቅም ያለው ሁሉ ዘመቻውን መቀላቀል እንዳለበት የጠቀሱት ተወያዮቹ፤ የአገር መከላከያ ሰራዊቱን ከመደገፍ ባለፈ በአሸባሪው ህወሃት የተፈናቀሉ ወገኖችን እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
ዘመቻውን የመደገፍ ስራው በተቀናጀ አግባብ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ሀገርን ማዳን ከአካባቢ ስለሚጀምር በአንድ መንፈስና ልብ የአሸባሪውን ቡድን አገር አፍራሽ ተላላኪዎች ማፅዳት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በውይይቱ የተወሰደው አቋምና እየተሰበሰበ የሚገኘው ድጋፍ አገር ለማዳን ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ተናግረዋል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።